Funny Amharic pipe dream about Boranticha and Ateete

ቦረንትቻ

 

ቦረንትቻ ግንቦት ወር ከገባበት ቀን ጀምሮ ወሩ እስኪጠናቀቅ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ማክሰኞ፣ ሀሙስና ቅዳሜ ቀናትን በመጠበቅ የሚከወን ሀገረሰባዊ ዕምነት ነው፡፡ ዕምነቱ ጠቋር በተባለ መንፈስ ለሚታዘዙ ‘ቦረን’ና ‘ትቻ’ ለተባሉ አባትና ልጅ ጭፍራ መናፍስት የሚቀርብ ግብር ሲሆን ቦረን ልጅ ትቻ ደግሞ አባት እንደሆኑ ይታመናል፡፡ ‘ቦረንትቻ’ የሚለውም ስያሜ ከነዚሁ ሁለት መናፍስት ስያሜ የተወሰደ ነው፡፡ እነዚህ እርኩስ መናፍስት ከብትን ብቻ የሚተናኮሉ ናቸው፡፡ ከብቶች እንዳይሞቱና እንዲረቡ እንዲሁም ጤነኛ እንዲሆኑ ለማድረግ በግንቦት ወር ጥቁር በግ ይታረዳል፡፡

 

ለግብሩ የሚያስፈልጉት ጥቁር በግ (አቅሙ ለፈቀደለት ሰው)፣ ድፎ ዳቦ፣ ቂጣ፣ የሽንብራ ቆሎ፣ በሶ፣ የስንዴ ቆሎ፣ የጠመዥ ቆሎ፣ የተወቀጠ ኑግ፣ ጉሽ ጠላ (ያልፈላ ጠላ) እና ብትን በርበሬ ናቸው፡፡ እነዚህ ዝርዝሮች የአካባቢው ማህበረሰብ በዋናነት የሚመገባቸው ነገሮች ናቸው፡፡ መናፍስቱም ሰዎቹ ከሚመገቧቸው ነገሮች ማግኘት ስላለባቸው እነዚህ ነገሮች በአግባቡ ተሰናድተው ለከበራው ይቀርባሉ፡፡

 

ቦረንትቻ የሚከበረው ከቤት ውጪ በከብቶች በረት አካባቢ ስለሚደረግ አስፈላጊው ዝግጅትም የሚደረገው በዚሁ ቦታ መሆኑን ምልከታ ባደረኩባቸው ሶስት ከበራዎች መረዳት ችያለሁ፡፡ ቦታው ከተጠረገና ቄጤማ ከተጎዘጎዘበት በኋላ ከላይ ቡናና የተጠቀሱት አስፈላጊ ነገሮች ይቀራርባሉ፡፡ ለሰዎች መቀመጫ የሚሆኑ መቀመጫዎች በክብ ቅርፅ ይዘጋጃሉ፡፡ ለቡና ማፍያና ለስጋ መጥበሻ የሚሆን ጊዚያዊ ምድጃ ይዘጋጃል፡፡

 

ቦረንትቻ እርድ በማድረግ (ደም በማፍሰስ)ና ያለ እርድ ሊከናወን የሚችል ሲሆን ስነስርዓቱ የሚከናወነው ከብቶች ወደበረት ከገቡ በኋላ ነው፡፡ እርድ የሚያከናውን ሰው ቤቱ ውስጥ ጥቁር በግ ከተወለደ ከቤት ካልተወለደ ደግሞ ከገበያ ገዝቶ ያርዳል፡፡ የእርድ ስነስርዓቱ ከመከናወኑ በፊት አባወራው በጉን ተሸክሞ ሶስት ጊዜ ቤቱን ይዞራል፡፡ ይህም በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ታቦት ወደማደሪያው ከመግባቱ በፊት በቤተክርስቲያኑ ዙሪያ ሶስት ጊዜ መዞሩን ተምሳሌት ያደረገ ነው፡፡ በመቀጠልም በጉ ከብቶች በረት አካባቢ ታርዶ ስጋው ውጪ በብረት ምጣድ ተጠብሶ ውጪ ይበላል፡፡ ውጪ የሚጠበሰው መናፍስቱ የስጋው ሽታ እንዲደርሳቸው በማሰብ ነው (ከአቶ ገብረመስቀል ገ/ጊዮርጊስና ከአቶ እሸቴ ነጋሽ ጋር በ11/09/2006 ዓ.ም. የተደረገ ቃለ ምልልስ)፡፡ ከታረደው በግና ቤት ውስጥ ተዘጋጅተው ከቀረቡት የሚበሉና የሚጠጡ ነገሮች በተጨማሪም ቡና ተፈልቶ ይጠጣል፡፡ ቡናው እንደየሰው ፍላጎት ቤት ውስጥ ወይም ከቤት ውጪ ሊፈላና ሊጠጣ ይችላል፡፡ ነገር ግን ውጪ ማፍላቱ የሚመረጥ ሲሆን ቡና የማፍላቱም ስነስርዓት ከወትሮው በተለየ መልኩ ቄጤማ ተጎዝጉዞ፣ ሰንደልና ዕጣን እየተጨሰ የሚደረግ ይሆናል፡፡

 

ለሰዎች ምግብነት የተዘጋጁት ነገሮች ሁሉ ከመቀመሳቸው በፊት ከሁሉም ነገር ትንሽ ትንሽ ተቆንጥሮ ለግብር ከተዘጋጁት (የተቆላ ድፍን ምስር፣ ሶስት ሪሚጦ፣ ጓያ፣ ጉሽ ጠላ) ጋር ለማባያነት ተጨምረው እንዲሁም ከሁሉም የበጉ ብልቶች ተቀንጥቦ በአሮጌ ዕቃ ወይም ገል (የሸክላ ስባሪ) ተደርጎ ፉካ (በከብቶች በረት ቆሻሻ ማስወገጃ አነስተኛ መስኮት) አካባቢ ይደረጋል፡፡ ይህም ከቦታው የማይነሳ ሲሆን የሚደረገው መናፍስቱ ወደ ከብቶቹ በረት በተጠጉ ጊዜ የሚቀምሱት ነገር ካገኙ ከብቶቹን አይተናኮሉም ተብሎ ስለሚታመን ነው፡፡ ካልተቀመጠላቸው ግን ወደከብቶቹ በረት ዘልቀው በመግባት ከብቶቹን ለሞት ሊዳርጉ፣ አካለ ስንኩል ሆነው አገልግሎት እንዳይሰጡ ሊያደርጉ፣ አመለኛ እንዲሆኑ ሊያነሳሱ ወይም እንዳይራቡ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ በፉካው በኩል የሚደረግው በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ አንደኛ መናፍስቱ የሰው እንቅስቃሴ በሚበዛበት አካባቢ አይገኙም፡፡ ስለዚህ በበር ከመግባት ይልቅ ሰው እንብዛም በማይንቀሳቀስበት ሰዋራ ስፍራ በመግባት ያጠቃሉ ተብሎ ይታመናል፡፡ ፉካም ቆሻሻ የሚወገድበት በመሆኑ የሰው እንቅስቃሴ በማይበዛበት በኩል ነው የሚሰራው፡፡ ሁለተኛ መናፍስቱ ከንፁህ ስፍራ በይበልጥ አመድ፣ አተላ፣ ፈርስና እበት የመሳሰሉ ቆሻሻዎች የሚጣሉበትን ስፍራ ይመርጣሉ፡፡ ፉካ ስር መደረጉም ለሁለቱም ምክንያቶች አመቺ ስፍራ ስለሆነ እንዲሁም ወደ እንስሳቱ ብዙም ሳይቀርብ መገኛው ስፍራ ድረስ ወስዶ እንደመስጠት ስለሚቆጠር ነው፡፡

 

ቦረንትቻው ያለ እርድ የሚከናወንም ቢሆን ስርዓተ ክዋኔው በተመሳሳይ ነው፡፡ በግ ሲቀር ሌሎቹ ነገሮች ሁሉ ተሟልተው ቡና ከቤት ውጪ (ግቢ ውስጥ) ተፈልቶ ቤተሰብ ተሰብስቦ አስፈላጊም ከሆነ ጎረቤትና ወዳጅ ዘመድ ተጠርቶ ይበላል፤ ይጠጣል፡፡ በዚህ ጊዜ ቡና ውጪ ማፍላት ግዴታ ነው፡፡ ምክንያቱም በግ ባለመታረዱ ውጪ የሚጠባበስና የሚሸተት ነገር ባለመኖሩ ቢያንስ የቡና ሽታ እንዲደርሰውና ለክብሩ የሚገባው ነገር በተገኘው አቅም ልክ እንደተደረገ ለማመላከት ነው፡፡

 

አቴቴ (ፈጫሳ)

 

በዚህ ጥናት ከተካተቱት ሀገረሰባዊ ዕምነቶች መካከል አምስተኛውና በመከወኛ ጊዜው የመጨረሻ የሆነው ሀገረሰባዊ ዕምነት አቴቴ (ፈጫሳ) ነው፡፡ አቴቴ በሴቶች የምትከወንና በሴት ፆታ የምትጠራ መንፈስ ስትሆን የተለየ ስርዓተ ክዋኔ ያላት ነች፡፡ አቴቴ የመንፈሷ ስያሜ ነው፤ የከበራ ሂደቱ ደግሞ ፈጫሳ ይባላል፡፡ ‘አቴቴ’ ቃሉ የኦሮሞኛ ቋንቋ ሲሆን ትርጓሜውም ጠባቂ/አዳኝ እንደማለት ነው (ደስታ ተክለወልድ: 1970፡605)፡፡

 

መኮንን ለገሰ አቴቴን በተመለከበተ በተጉለትና በቡልጋ አውራጃ በሰራው ጥናት ውስጥ ፍሰኃ ኃ/መስቀልን (1975) ጠቅሶ አቴቴ ሐራ፣ አቴቴ ግንቢ፣ አቴቴ ዱላ፣ አቴቴ ዱበራ፣ አቴቴ ቦረና፣ አቴቴ ወርቄና አቴቴ ጉራጌ የሚባሉ ሰባት ራሳቸውን የቻሉ የአቴቴ መናፍስት እንዳሉ በመግለፅ በእርሱ ጥናት አካባቢ ግን አቴቴ ሀራ፣ አቴቴ ግንቢ፣ አቴቴ ዱላና አቴቴ ወርቄ የሚባሉት ብቻ እንደሚታወቅ ጠቁሟል (1982፡ 8)፡፡ በዚህ ጥናት ውስጥ ተተኳሪው አካባቢ ግን አቴቴ በመንፈስ አንድ ስትሆን ሶስት መጠሪያ ስሞች አሏት፡፡ ይህ የሚያሳየው እንደየ ማህበረሰቡ አረዳድ በየአካባቢው የሚኖሩት አቴቴዎች በስያሜም በቁጥርም ሊለያዩ ይችላሉ፡፡

 

የአቴቴን ከበራ አጀማመር በተመለከተ የተለያዩ ምንጮች የተለዩዩ ነጥቦችን ያነሳሉ፡፡ ለአብነት ያህል ደስታ ተክለወልድ ባዘጋጁት መዝገበ ቃላት ውስጥ ‘ጨሌ’ የሚለውን ቃል ሲፈቱ መነሻው ህንድ አገር እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡ የአንዳንድ ነገዶች ባላባቶችና ሚስቶቻቸው ሀፍረተ ስጋቸውን ለመሸፈን ይጠቀሙበት እንደነበረና ‘አረማውያን’ የግንብ፣ የውሃና የዘመቻ አምላክ ተደርገው ይመለክባቸው እንደነበረ እንዲሁም የአማራው ማህበረሰብ ከኦሮሞ ማህበረሰብ እንደወረሰው ይገልፃሉ (1970፣149 እና 605)፡፡ በዚህ ጥናት ተተኳሪ የሆነው አካባቢ ማህበረሰብም ለዕምነቱ ከየት መጣነት የሚቀጥለውን ቃላዊ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

 

ከቀይ ባህር ነው የመጣችው፡፡ ከዚያ በኋላ ከዛፍ ላይ አረፈች በቀይ ባህር ዛፍ ላይ፡፡ ….. ውቃቢዎች እንደ እናት አድርገው ያምኑባታል፡፡ አቴቴ ግንቢ፣ አቴቴ ዱላ፣ አቴቴ ሃራ እያሉ እንደ ሶስቱ ስላሴዎች ያምኑባታል፡፡ ይህንን ተከትለው ህዝብ ሁሉ ያምኑባታል፡፡ እሷ ግን የምትገኘው ከዛፍ ላይ ነው ያለችው፡፡ የቀዬው ሰዎች ቀይ ባህርጋ ከሚገኘው ላይ ፍሬ ለቅመው ለአምልኮ እንዲመቻቸው ቀይ፣ አረንጓዴ፣ ነጭና ዶቃ እንዲሁም ዝም ብሎ ይቀባል፡፡ ለእያንዳንዱ ስም ይሰጡታል፡፡ ከዚያ ወዲህ በሶስቱ ስም ይታመንበታል (ከወ/ሮ አየለች ስንሻው ጋር በ18/11/2006 ዓ.ም. የተደረገ ቃለ ምልልስ)፡፡

 

ጥቅሱ በማህበረሰቡ አረዳድ የአቴቴ መንፈስ በዛፍ ላይ የምትገኝ ሲሆን የመጣችው ከቀይ ባህር ውስጥ መሆኑን በግልፅ ያሳያል፡፡ በዛው በቀይ ባህር አካባቢም አርፋበታለች ተብሎ ከሚታመነው ዛፍ ላይ ፍሬዎችን በመልቀምና ቀይ፣ አረንጓዴ፣ ነጭና ዶቃ (ጥቁር ሰማያዊ) ቀለሞችን በመቀባት የዕምነቱ ክዋኔ እንደተጀመረ ከማህበረሰቡ ምላሽ መረዳት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ይህ ማህበረሰቡ ዕምነቱ ከየት እና እንዴት ተጀመረ ለሚሉት ጥያቄዎች የሚሰጠው ምላሽ ይህ ሀሳብ ደስታ ተክለወልድ አጀማመሩን በተመለከተ ካሰፈሩት ሀሳብ የተለየ ነው፡፡ ቢሆንም ግን ምናልባትም ለህንዳውያኑም መነሻቸው ይኸው ቀይ ባህር ይሆናል የሚል እሳቤ በማህበረሰቡ ዘንድ አለ፡፡ ከህንዳውያኑ ደግሞ ደስታ ተክለወልድ በጠቀሱት መንገድ በሀገራችንም ተሰራጭቶ አሁን ያለበት ደረጃ ደርሷል (ከአቶ ሀይሉ እሩፌ ጋር በ19/11/2006 ዓ.ም. የተደረገ ቃለ ምልልስ)፡፡

 

እንደ አካባቢው ማህበረሰብ ዕምነት አቴቴ ወቅት ተጠብቆ ፈጫሳ ካልተከበረላት የህፃናትን፣ የአዛውንቶችንና የሴቶችን ጤንነት ትፈታተናለች፡፡ የእነዚህን ደህንነታቸውን ለመጠበቅም ከበራው በጥቅምት፣ በታህሳስ፣ በሚያዚያና በሀምሌ ወራት ይካሄዳል፡፡ በአካባቢው በአብዛኛው አቴቴ የምትከበረው በሀምሌ ወር ሲሆን ለከበራውም ማክሰኞ፣ ሀሙስና ቅዳሜ ቀናት ቅዱስ ቀናት እንደሆኑ ያታመናል፡፡

 

አቴቴ የሚከወንበት ቤት አዘውትረው ምግብ የሚያበስሉበት፣ የሚመገቡበትና ብዙ ጊዜያቸውን የሚያሳልፉበት ቤት ወይም ጫት ቅቀላና ለጭዳ በሚዘጋጀው አነስተኛ ጎጆ ቤት ውስጥ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን እኔ ምልከታ ባደረኩባቸው ሶስቱም ክዋኔዎች የተከወኑት ሁልጊዜም በሚጠቀሙበት ቤት ውስጥ ነው፡፡ ቤቱ ዘወትር የሚጠቀሙበት ቢሆንም ለዚህ ዕለት የተለየ የቤት ዝግጅት ያስፈልጋል፡፡ በተገኘሁባቸው ሁሉም ክዋኔዎች ላይ ይህንኑ መመልከት ችያለሁ፡፡ ስርዓተ ክዋኔው የሚደረገው ቅዱስ ቀናት ናቸው ተብሎ ከሚታመንባቸው መካከል አመቺ የሆነውን በመምረጥ ሲሆን አመሻሽ ላይ ከብት ከገባ በኋላ ይደረጋል፡፡

 

የአቴቴ ክዋኔን በተመለከተ ሰፊ መረጃ ያገኘሁበት ወ/ሮ ፈለቀች አልታዬ ቤት ማክሰኞ ቀን የተደረገው ነው፡፡ ከዋኟ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት አካባቢ አቴቴ የሚሉበትን ቤት ለከበራው በሚያመች መልኩ ያሰናዱታል፡፡ ይህን ክዋኔ ያደረኩበት ቤት ምድር ቤት እና ዘወትር ለምግብ ማብሰያነትና መመገቢያነት የሚጠቀሙበት ሲሆን በአማካኝ 7 ሜትር በ5 ሜትር የሚሆን ስፋት አለው፡፡ ቤቱ ምድር ቤት እንደመሆኑ መጠን ጣሪያው ላይ የላይኛው ፎቅ ቤት ርብራብ በጉልህ ይታያል፡፡ መግቢያ በሩ በስተ ምዕራብ አቅጣጫ የሚገኝ ሲሆን ከበሩ በስተቀኝ አንድ አነስተኛ በቀርከሃ የተከፈለ ክፍል (ጓዳ) ይገኛል፡፡ በግድግዳው ስር ዙሪያውን መደብ በመኖሩ ታዳሚዎች እዛ ላይ ይቀመጣሉ፡፡ ከበሩ በስተግራ በኩል ባለው ግድግዳው ላይ ደግሞ አንድ ቆጥና ሁለት ዘረንጋዎች ይገኛሉ፡፡ ቆጡ ላይ የማገዶ እንጨት በጪስ እንዲደርቅ ተደርድሮበታል፡፡ ከሁለቱ ዘረንጋዎች መካከል አንዱ በምዕራባዊ ግድግዳው ላይ የሚገኝ ሲሆን የተለያዩ አነስተኛ መጠን ያላቸው መገልገያ ቅሳቁሶች ተደርድረውበታል፡፡ ሁለተኛው ዘረንጋ በደቡባዊው ግድግዳ ላይ ሲገኝ ከዋኟ ተቀምጠው ለሚሰሩበት ምድጃ ቅርብና ለምግብነት እንዲሁም ለክዋኔው የሚያገለግሉ ነገሮች የተደረደሩበት ነው፡፡

 

ቤቱ አስፈላጊው ፅዳት ተደርጎለታል፡፡ በቤቱ በምስራቃዊና በደቡባው ግድግዳዎቹ መጋጠሚያ ስር በክብ ቅርፅ መሬት ላይ በተሰራው ምድጃ ዙሪያ እርጥብ ቄጤማ ተጎዝጉዞ ቡና ቀራርቧል፡፡ ከዋኟ ከምድጃው እሳት ለመገልገልና ሌሎቹን የአቴቴ ክዋኔዎች ለማድረግ በሚያመቻቸው መልኩ በምድጃው ዙሪያ በተሰራው መደብ ላይ ተቀምጠው ለክዋኔው የተዘጋጁትን ነገሮች ያቀራርባሉ፡፡ ክዋኔውን ለመመልከትና ለመሳተፍ በቦታው የነበርነው 7 ሰዎች ስንሆን 3ቱ ልጆቻቸው፣ 2ቱ የልጅ ልጆች፣ 1 የእኔ ረዳትና እኔ ነበርን፡፡

 

ለክዋኔው የሚያስፈልጉት ሁለት ማሰሮ ቅንጬ፣ የቀለጠ ቅቤ፣ ሶስት ድፎ ዳቦ፣ ቂጣ፣ ሰባት ድፍን ቡና፣ ጭሳጭስ (ድኝ፣ ከርቤና ሌሎች የጭስ አይነቶች የተቀላቀሉበት)፣ ጠላ፣ ጠጅ ሳር፣ ሽቶ ሳር እና የሚፈላ ቡና ሲሆኑ ሁሉም በምድጃው ዙሪያ በተጎዘጎዘው ቄጤማ ላይ ይቀርባሉ፡፡ በጫት ቅቀላና በጭዳ ወቅት እንደሚደረገው ሁሉ በዚህም ዕምነት ውስጥ አምልኮው የሚደረገው በምሰሶ ስር ነው፡፡ ስለዚህ ክዋኔው የሚደረግበት ቦታ ከምሰሶው ባይርቅ ይመረጣል፡፡

 

ከዚህ በኋላ የከበራ ክዋኔውን መጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡ አቴቴ ለከበራ ቀኗ ብቻ የሚለበስ የክብር ልብስ አላት፡፡ ልብሱ ከጥጥ ፈትል የተዘጋጀ ጥቁር ጥለት ያለው ጥብቆ (ቁመቱ ከጉልበት የማያልፍ ቀሚስ)ና ከአንደኛው ጫፍ ጥቁር ጥለት ከሌላጫው ጫፍ ደግሞ ቀይ ጥለት ያለው የአንገት ልብስ ሲሆን ከከበራው በኋላ እስከ ቀጣዩ ከበራ ድረስ በክብር ተጠቅልሎ ሳጥን ውስጥ ይቀመጣል፡፡ ከልብሱ በተጨማሪም አቴቴ የምትመለክበት ዋነኛ መሳሪያዎች ሶስት ጨሌዎች ናቸው፡፡ ከዋኟ የክብር ልብሷን ከተቀመጠበት አውጥተው ከለበሱ በኋላ ጨሌዎቹ የቀለጠ ቅቤ ተነክረው አንገት ላይ ይጠለቃሉ፡፡ ነገር ግን የአቴቴ ከበራውን እራሳቸው ካልጀመሩት (ከቤተሰብ ከወረሱት) የክብር ልብሱን መልበስም ሆነ ጨሌዎቹን አንገት ላይ ማድረግ አይገደዱም፡፡

 

ጨሌዎች የሚዘጋጁት በባህር ውስጥ ከሚገኝ ባልጩት የሚባል የድንጋይ አይነት ነው፡፡ ሶስቱም የተለያየ ቀለማት እና ስያሜዎች አሏቸው፡፡ በቁመት ከሁለቱ በተወሰነ መጠን ረዘም የምትለው ጥቁር ሰማያዊና ነጭ ቀለማት ካላቸው ዶቃዎችን የተዘጋጀች ስትሆን ስያሜዋም አቴቴ ግንቢ ይባላል፡፡ አረንጓዴ ቀለም ያላት ጨሌ አቴቴ ሐራ ስትባል ጥቁር ሰማያዊ፣ ነጭና ቀይ ቀለማት ካላቸው ጨሌዎች የምትዘጋጀው ደግሞ አቴቴ ዱላ በመባል ትታወቃለች፡፡ በቁጥር ይከፋፈሉና ገመዱ ይቋጠራል ወይም በመጠን ከፍ ያለ ዶቃ ይደረግበታል፤ ይህ መክተሪያ የሚባል ሲሆን በቁጥር የተለዩት ዶቃዎች እንዳይቀላቀሉ የሚያደርግ ነው፡፡ እነዚህን ዶቃዎች ቁጥር አመጣጥኖ የሚከትር፣ የሚያስርና ትርጓሜያቸውንም የሚያውቅ ሰው ጨሌ አሳሪ ይባላል፡፡

 

እርጥብ ሳር በተጎዘጎዘበት ወንፊት ላይ የቀለጠ ቅቤ በጣባ (ትንሽ ሳህን መሳይ ሽክላ) ተደርጎ ይቀርባል፡፡ እጣኑና ሰንደሉ በደንብ ከተጨሰ በኋላ ጨሌዎቹ የጣባው ቅቤ ውስጥ ሶስት ጊዜ ይነከራሉ፡፡ ቅቤ ከተነከሩ በኋላ በአቴቴ ግንቢ፣ ሓራና ዱላ የተሰየሙት ጨሌዎች በቅደም ተከተላቸው መሰረት አንገት ላይ ይነገታሉ፡፡ በመቀጠል ለከዋኟ ጨሌዎቹ በቀረቡበት ወንፊት ላይ ሳህን ተደርጎ የቀለጠ ቅቤ እና የተቆሉት ሰባት ድፍን ቡናዎች መካከሉ ላይ ተጨምሮበት ይቀርባል፡፡ ከወንፊቱ ላይም ሶስት ሳሮችን በቀኝ እጅ ሶስቱን ደግሞ በግራ እጅ በመያዝ ከቅንጬው ላይ በሳሩ ቅቤ እየተነከረ አንገት ላይ የተንጠለጠሉት ጨሌዎች ሶስት ግዜ ይቀባሉ፡፡ ይህን በሚያደርበት ወቅት ‘‘እሊሊሊሊሊሊ…. አቴቴ ግንቢ አቴቴ ሐራ አቴቴ ዱላ በሳርሽ በለምለምሽ በጨፌሽ ልጆቹንም ከብቶቹንም ቀዬውንም ጠብቂ ለአመቱ ደግሞ በሰላም ካደረስሽን ከዚህ በላይ ደግሰን እናከብርሻለን’’ እያሉ ያመሰግኗታል ይለምኗታልም፡፡ ከዋኟ ቡናዎቹን በጥርሳቸው እየሰባበሩ ወንፊቱ ላይ ወደሚገኘው ሳር ይበትኑታል፡፡ ትርጓሜውም ችግራችንን እንደዚህ አድቅቀሽ አስወግጂልን እንደማለት ነው፡፡

 

የተቀቀለው ቅንጬም ከሁለቱም ማሰሮዎች ተቀንሶ ለተሳታፊዎቹና ለከዋኟ ይቀርባል፡፡ ሁሉም ሰው ከመቅመሱ በፊት ለከዋኟ ከቀረበው ላይ መጀመሪያ ለመንፈሷ ሶስት ጊዜ ተቆንጥሮ ይጣል፡፡ ከመንፈሷ ቀጥሎ ከዋኟ ይቀምሱና ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት እንዲመገቡ ይደረጋል፡፡ ቡናና ጠላ እየተጠጣ ቅንጬው ይበላል፡፡ የጨሌዋ አምላክ ትቃጠላለች ተብሎ ስለሚታሰብ በርበሬና ጨው ነክ ነገር በክዋኔው ላይ ለምግብነት አይቀርብም፤ ከዋኟም መመገብ የለባትም፡፡

 

በምሽት አቴቴ ግንቢ አቴቴ ሐራ አቴቴ ዱላ ተብላ የተጠራችው መንፈስ ልጆቹንና ከብቶቹን በምህረት ስትጎበኝ ታድራለች፡፡ በማግስቱ ጠዋት ቡና ተፈልቶ፣ አንድ ድፎ ተቆርሶ ከሶስት ሪሚጦዎችና ኑግ ተደርጎ ማታ የተጎዘጎዘው ቄጤማ ተጠርጎ ይጣላል፡፡ ይህ ሂደት መንፈሷን መሸኛ ሲሆን ጨሌ ጠረጋ ይባላል፡፡ ጠረጋው ሲጠናቀቅ ለጨሌዎቹ ማስቀመጫነት በተዘጋጀው አነስተኛ ሙዳይ ውስጥ ሽቶ ሳር፣ ጠጅ ሳርና ቅቤ ተደርጎበት ይከተቱና ለቀጣዩ ከበራ ይቀመጣሉ፡፡

 

ከወ/ሮ እቴነሽ ጋር ባደረኩት ቃለ ምልልስ አቅም ያላቸው ሰዎች ለአቴቴ ቀይ ሴት በግ የሚያርዱ ቢሆንም ይህ በብዛት አይታይም፡፡ እኔም በምልከታዬ ይህንን አልተመለከትኩም፡፡ ነገር ግን ከበራውን ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ ጨሌ የሚያደርጉ ሰዎች ግዴታ እንደሆነ ገልፀውልኛል፡፡ ምክንያቱም በጨሌዎቹ ላይ የምታድረው መንፈስ እንድትለምድ ጨሌዎቹ በቀይ ሴት በግ ደም መነከር አለባቸው፡፡ አንዳንዶች ጨሌዎቹን ብቻ ሳይሆን ራሳቸውም በዚሁ ደም እንደሚነከሩም ገልፀውልኛል፡፡

 

አቴቴን የሚከውን ሰው ስርዓተ ክዋኔውን ማቋረጥ ከፈለገ ስርዓቱን ተከትሎ መሆን አለበት፡፡ ሁለት አይነት የማቋረጫ መንገዶች አሉ፡፡ አንደኛው ጨሌዋን ለሚፈልጉ ሰዎች መሸኛ ሁለት ቁና እህልና ሃያ ብር አድርጎ መስጠት ሲሆን ሁለተኛው ውሃ ወይም እሳት ውስጥ መጨመር ሲሆን ከዚህ በኋላ የጨሌዋ መንፈስ በእነርሱ ላይ ስልጣን እንደሌላት አጠንክረው የሚገልፁበት መንገድ ነው፡፡ የመጀመሪያው ተመራጭ መንገድ ነው፡፡ ምክንያቱም ሰላማዊ ባልሆነ መንገድ ፈጫሳን ማቋረጥ በአዛውንቶችና በልጆች በተጨማሪም በከብት ላይ ችግር ያስከትላል ተብሎ ይታመናል፡፡ የሚያስከትለው ችግር በከብቶች ላይ የመራባት ሂደትን ይቀንሳል እንዲሁም ለሞት ይዳርጋል፤ በልጆች ላይ ደግሞ የአይንና የልብ በሽታዎችን ያስከትላል በተጨማሪም ትዳር እንዳያገኙ ያደርጋል ተብሎ ይታመናል (በ15/11/2006 ዓ.ም. የተደረገ ምልከታና ከወ/ሮ ፈለቀች፣ ከወ/ሮ ሙላቷና ከአቶ ዘውዴ ጋር የተደረገ ቃለ ምልልስ)፡፡

Post your comment

Comments

Be the first to comment

Related Articles