‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች የእዚህን መንግሥት መሠረታዊ እምነቶች ተረድተው ስኬቶቹንና ድክመቶቹን መገምገም አልቻሉም›› ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ

 

 

 

 ዘ አፍሪካ ሪፖርት፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ሒደት የሚያሳልጡት ምንድን ናቸው?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- ልዩ ጥቅማችንንና ከሌሎች በልጠን የምንገኝባቸውን ሀብቶቻችንን እየተጠቀምን ነው፡፡ በጣም ወጣት የሆነ ሕዝብ ነው ያለን፡፡ መሬት በተትረፈረፈ መጠን አለን፡፡ ርካሽ የሆነ የአሌክትሪክ ኃይል አለን፡፡ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን፣ ቅድሚያ ለምንሰጣቸው የኢንዱስትሪ ዘርፎች የተለያዩ ድጋፎችን የምናደርግ ሲሆን፣ ፖሊሲያችንን መሠረት ባደረጉ ባንኮቻችን አማካይነት የገንዘብ ድጋፍ ጭምር እንሰጣለን፡፡

ዘ አፍሪካ ሪፖርት፡- በእስያ የነበሩት ልማታዊ መንግሥታት ኮርፖሬሽኖችን በመምራት ረገድ በጣም ንቁ ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ይህ የማስተዳደር አቅም አለ?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- በጃፓን የነበረው የንግድና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በጣም ጠንካራ ነበር፡፡ ነገር ግን በደቡብ ኮሪያ ይኼን ሒደት የሚደግፉ በርካታ ተቋማት ነበሩ፡፡ ሁሉንም ነገሮች በአንድ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የመምራት አቅም ስለሌለን የኮሪያን ሞዴል ተከትለናል፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ክህሎት ማዳበርና ቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ የሚሠሩ እንዲሁም መንግሥት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን እንደ ጨርቃ ጨርቅ፣ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች፣ ምግብና ለስላሳ መጠጦች፣ የኬሚካል ኢንዱስትሪዎች የመሳሰሉ ዘርፎችን የሚያግዙ በርካታ ተቋማት አሉ፡፡

ጥቂት ኢንዱስትሪዎችን ከጅምራቸው እስከሚጠናከሩ ድረስ የሚከታተሉ የባለሙያዎችን ቡድኖችም እንመድባለን፡፡  በአሁኑ ጊዜ ይኼን በራሳችን ሙሉ በሙሉ ለመፈጸም የአቅም ውስንነት ስላለ ባለሙያዎችን ከውጭ እናስመጣለን፡፡ የኮሪያ የልማት ኢንስቲትዩት በዚህ ረገድ በጣም እያገዘን ነው፡፡ ህንድም ከጨርቃ ጨርቅና ከቆዳ ውጤቶች ዘርፎች ጋር በተገናኘ ድጋፍ እያደረገችልን ነው፡፡ በልማት ስኬታማ ከሆኑ አገሮች ጋርም ተቋማዊ ግንኙነት መስርተናል፡፡ 

ዘ አፍሪካ ሪፖርት፡- በደቡብ ኮሪያ የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ለማሳካት አንድ ትውልድ መስዋዕት ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያዊያን ይኼን ለማድረግ ዝግጁ ናቸው?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን በዚህ ሒደት አብረውህ እንዲሆኑ የግድ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ነገር ግን የአብዛኛውን በተለይም የወጣቱን ድጋፍ ትፈልጋለህ፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ሥርዓታችንን ካየን 70 በመቶው የሚመረቀው በኢንጂነሪንግና በሳይንስ ሲሆን፣ በማኅበራዊ ሳይንስ የምናስመርቀው 30 በመቶውን ብቻ ነው፡፡ ይኼ ማለት 70 በመቶው ተመራቂ የኢንዱስትሪ ሽግግር ሒደቱ ላይ ይሳተፋል ማለት ነው፡፡ በተመሳሳይ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መግባት የማይችሉ ተማሪዎች ሁሉም ማለት ይቻላል ወደ ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ነው የሚገቡት፡፡ ኢትዮጵያ ወዴት መሄድ እንዳለባትና ምርታማነትን ለመጨመር የአሁኑ ትውልድ መክፈል ስላለበት መስዋዕትነት የማሳመን ሥራ እየሠራን ነው፡፡ ዋናው ነገር የቀድሞውን አስተሳሰብ መቀየር ነው፡፡ ተወዳዳሪ ለመሆን እጅግ አስፈላጊ የሆኑትን ምርታማነትንና ጥራትን መሠረት ባደረገው ንቅናቄ ሁሉም ተሳታፊ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ ወጣቱ ትውልድ በብሔራዊ ደረጃ ይኼ አስተሳሰብ እንዲኖረው ለማድረግ ወደ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በቀጣይነት እንወርዳለን፡፡  

ዘ አፍሪካ ሪፖርት፡- በአገሪቱ እየተከናወኑ ያሉ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችን ወጪ መሸፈን ከባድ ነው፡፡ አማራጮቻችሁ ምንድን ናቸው?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- በመጀመሪያ የአገር ውስጥ የፋይናንስ ምንጮችን ለመጠቀም እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ በቅርብ ዓመታት ልማታዊ መንግሥታት የነበሩ እንደ ቻይና ያሉ አገሮችን ልምድ ካየን ዋነኛ የፋይናንስ ምንጫቸው ብሔራዊ ቁጠባቸው ነበር፡፡ በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ውስጥ አበረታች አዝማሚያን እያየን ነው፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችን ሲጠናቀቅ ከአጠቃላይ ብሔራዊ ምርት ስድስት በመቶ ድርሻ የነበረው ብሔራዊ ቁጠባ ወደ 15 በመቶ ያድጋል ብለን እናስብ ነበር፡፡ ነገር ግን በሚገርም ሁኔታ ከዕቅዳችን በላይ በመሄድ የዕቅዱ ሦስተኛ ዓመት ሳይጠናቀቅ አስቀድሞ 17.7 በመቶ ደርሷል፡፡ ስለዚህ ዕቅዳችንን ከልሰን ዕቅዱ ሲጠናቀቅ 20 በመቶ ለመድረስ እየሠራን ነው፡፡ ይኼ ጊዜ ሕዝባችን ጥቂት እያወጣ ብዙ እንዲቆጥብ የምንጫንበት ነው፡፡ 4.6 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣውን የታላቁ ህዳሴ ግድብ እየገነባን ያለነው ከዚህ ቁጠባ ነው፡፡ ሕዝቡ በነፃ ማዋጣት ፈልጎ ነበር፡፡ ነገር ግን እኛ ‘የቁጠባ ባህል ለማዳበር ቦንድ መግዛት አለብህ’ ብለነዋል፡፡

ነገር ግን ይኼ በቂ አይደለም፡፡ አሁንም ቢሆን የፋይናንስ እጥረት ስላለብን ከብራዚል፣ ከህንድ፣ ከቻይና፣ ከቱርክ፣ ከጃፓንና ከኮሪያ ኢንቨስትመንት መሳብ ችለናል፡፡ ተመራጭ በሆነ የቁጠባ ወለድ መጠን ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት በማድረግ ያገኙትን ገቢ እዚሁ እንዲቆጥቡ እያደረግን ነው፡፡ ለንግድ እንቅስቃሴያችንም ብድር እንፈልጋለን፡፡ ብድር የመመለስ አቅም ደረጃ ለማግኘት እየሠራን ሲሆን ሒደቱ በጥሩ ሁኔታ እየሄደ ነው፡፡ [ሆኖም ከቃለ መጠይቁ በኋላ የኢትዮጵያ የብድር የመመለስ አቅም ውጤት የታወቀ ሲሆን በአማካይ ‘B’ ማግኘቷን መዘገባችን ይታወሳል]

ዘ አፍሪካ ሪፖርት፡- የኢትዮጵያ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን እየተጫወተ ካለው ሚና ጋር በተያያዘ የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ለመምራት ወታደሮች የተሻሉ ሰዎች ናቸው ብለው ያስባሉ?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- የብዙ አገሮች ወታደራዊ ተቋማት ያሏቸውን በጣም ጥሩ ላብራቶሪዎችና ወርክሾፖችን ለወታደራዊ ዓላማ ብቻ ይጠቀሙባቸዋል እንጂ ለልማት ዓላማ ሲጠቀሙባቸው አይታይም፡፡ እኛ ግን ወታደራዊ ተቋሞቻችን ያላቸውን አቅም ለሲቪል ልማት እንጠቀማለን፡፡ በሜካኒካል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ያለውን ታሪክ ካየን ብዙ ነገሮች የመጡት ከወታደራዊ ተቋማት ነው፡፡ ስለዚህ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽንን አቅምና ዲሲፕሊን እየተጠቀምን ነው፡፡ ይኼ ማለት ግን በኢንዱስትሪ ጉዳይ ብቸኛው ተቋም ነው ማለት አይደለም፡፡ ነገር ግን የመሪነት ሚና ይጫወታል፡፡ የተለያዩ የግሉ ዘርፍ አካላት አብረውት ይሠራሉ፡፡ በሒደት ከትልልቅና ከትናንሽ ከግሉ ዘርፍ ከመጡ የኢንጂነሪንግ ኩባንያዎች ጋር በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡ 

ዘ አፍሪካ ሪፖርት፡- በ2007 ዓ.ም. በሚደረገው ብሔራዊ ምርጫ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በርካታ የፓርላማ መቀመጫዎችን ያሸንፋሉ ብለው ይጠብቃሉ?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- እኛ ማተኮር የምንፈልገው በሒደቱ ላይ ነው፡፡ ሒደቱ ዲሞክራሲያዊ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊና በሕዝቡ ዓይን ተዓማኒ የሆነ እንዲሆን ማድረግ አለብን፡፡ ውጤቱን የሚወስነው መራጩ ሕዝብ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወይም ኢሕአዴግ ይኼን ያህል ወንበር ያሸንፋሉ ብዬ መገመት አልችልም፡፡ 

ዘ አፍሪካ ሪፖርት፡- ሒደቱ ዲሞክራሲያዊ ነው ብለው ያስባሉ?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- ተቋማዊ አሠራራችን፣ ሕጎቻችንና ደንቦቻችን እንከን አይወጣላቸውም፡፡ ከሕጎቻችን በተቃራኒ አፈጻጸም ላይ ነው ወደኋላ የቀረነው፡፡ የፓርቲዎች የሥነ ምግባር ደንብን ተፈጻሚ አድርገናል፡፡ በዚህ ደንብ ብንመራ ሒደቱን የተሻለ ዲሞክራሲያዊ፣ ነፃ፣ ፍትሐዊና ተዓማኒ ለማድረግ ይጠቅማል ብዬ አስባለሁ፡፡

ዘ አፍሪካ ሪፖርት፡- እንደ 2002 ዓ.ም. ብሔራዊ ምርጫ ውጤቱ ለተቃዋሚ ፓርቲዎች አንድ ወንበር ብቻ በማግኘት ቢጠናቀቅ የመንግሥት ተዓማኒነት ላይ ጉዳት አያመጣም?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- አይመስለኝም፡፡ ውሳኔው የተሰጠው በሕዝቡ ከሆነ ሁላችንም ልንቀበለው ይገባል፡፡ አንዳንዴ የሚረብሸን እንኳን ቢሆን የግድ መቀበል መቻል አለብን፡፡

ዘ አፍሪካ ሪፖርት፡- ገንቢ ትችቶችን የሚያቀርብ ተቃዋሚ ፓርቲ ፓርላማ ቢኖር ጥሩ አይሆንም?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- የሥነ ምግባር ደንቡ የተቀረፀው የፓርላማ ምርጫው የነበረበትን ጉድለት ለመቅረፍ ነው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ኢሕአዴግ በሰፋ ልዩነት አሸንፏል፡፡ ነገር ግን ሦስት ሚሊዮን ከሚጠጉ ነዋሪዎች ውስጥ 400,000 መራጮች ድምፃቸውን ለተቃዋሚዎች ነው የሰጡት፡፡ የእነዚህ 400,000 ሰዎች ድምፅ ሊሰማ ይገባል፡፡ እንዴት አድርገን ድምፃቸውን እንስማ? ይኼን ለመመለስ የሚያስችል የፓርቲዎች የጋራ ምክክር መድረክ አለን፡፡ ፓርላማው በሕግና በፖሊሲ ላይ ከመወያየቱ በፊት በምርጫ የተወዳደሩ ፓርቱዎች በጋራ አስቀድመው እንዲወያዩበት ዕድል ያገኛሉ፡፡

ራሳችንን በእነሱ በኩል ለማየት ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲኖሩ እንመኛለን፡፡ ከእኛ ውጪ ያለ አካል ቢተቸን እንወዳለን፡፡ ያለመታደል ሆኖ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ ተቃዋሚዎች የሉንም፡፡ ግልጽ የሆነ የራሳቸው ፖሊሲ ያላቸው ፓርቲዎች የሉም፡፡ የእዚህን መንግሥት መሠረታዊ እምነቶች ተረድተው ስኬቶቹንና ድክመቶቹን ለመገምገም አልቻሉም፡፡ ኢሕአዴግን የብጥብጥ መንገዶችን ተከትለው ከሥልጣን ማስወገድና ወደ ሥልጣን መምጣት ይፈልጋሉ፡፡ ይኼ የማይሳካ ምኞት ነው፡፡  

ዘ አፍሪካ ሪፖርት፡- የደቡብ ሱዳን ግጭት አካባቢውን የሚነካ በመሆኑ አልተጨነቁም?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- በኢጋድ አካባቢ ግጭቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት ለማድረግ አብሮ ለመሥራት ተስማምተናል፡፡ ከአካባቢው ወደ ደቡብ ሱዳን የሚላከው ኃይል ጥበቃ ከማድረግም ባሻገር ለሌሎች የጥፋት ኃይሎች ተመሳሳይ ስህተት እንዳይደገም ትምህርት ይሰጣል፡፡ ሱዳንና ኡጋንዳ የዚህ ኃይል አባል ላለመሆን ተስማምተዋል፡፡ ይኼ አካባቢያዊ ግጭትን ያስወግዳል፡፡ ነገር ግን የዚህን ኃይል ሥራ ማፋጠን አለብን፡፡

ዘ አፍሪካ ሪፖርት፡- በኡጋንዳ ጣልቃ መግባት ላይ የኢትዮጵያ አቋም ምንድን ነው? ጉዳዩን አወሳስቧል ብለው ያስባሉ?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- ጉዳዩን አላወሳሰበውም፡፡ ኡጋንዳ ጣልቃ ባትገባ ኖሮ አሁን በደቡብ ሱዳን ያለውን መንግሥት ማየት ስለማንችል እንዲያውም ጣልቃ መግባቷ ጠቃሚ ነበር፡፡ አለበለዚያ የደቡብ ሱዳን መንግሥት ወዲያው ነበር የሚፈርሰው፡፡ ሱዳንና ኡጋንዳ ያሉዋቸው የተለያዩ አመለካከቶች በተግባር ችግር እንዳይፈጥሩ ኡጋንዳ በሒደት ከደቡብ ሱዳን እንድትወጣ እንፈልጋለን፡፡ ሱዳንም አዲስ በሚዋቀረው ኃይል ተሳትፎ እንድታደርግ አንፈልግም፡፡  

ዘ አፍሪካ ሪፖርት፡- ደቡብ ሱዳን ነፃ ስትወጣ ከመጠን ያለፈ ደስታ ነበር፡፡ አሁን ነገሮች ከያዙት ገጽታ አኳያ ሁኔታዎቹ አያበሳጩዎትም?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- ይኼ እንደሚሆን ጠብቀን ነበር፡፡ ስለዚህ አልተበሳጨሁም፡፡ አቅጣጫቸውን እየረሱ ነበር፡፡ ለአዲሷ አገር የነበራቸው ፖሊሲ በአግባቡ የተቀረፀ አልነበረም፡፡ ሒደቱን ማን እንደሚመራው ራሱ በግልጽ ያልተቀመጠ ሲሆን ተቋማዊ ግንባታውም ተዘንግቶ ነበር፡፡ 100 ቴክኒሻኖችንና ቢሮክራቶችን ወደ ደቡብ ሱዳን ልከን ነበር፡፡ ተቋማዊ ግንባታውን ለማገዝ የተለያዩ ስምምነቶችን ተፈራርመን ነበር፡፡ በተለይ የጋራ የመሠረተ ልማት ግንባታ ለማካሄድ ተስማምተን ነበር፡፡ ነገር ግን እኛም ከስህተታችን ተምረናል፡፡ የእኛን ተሞክሮ ልናካፍላቸው እንፈልጋለን፡፡ አማፂያን መንግሥት ሲሆኑ ተገቢ የሆነ ሽግግር መካሄድ አለበት፡፡ 

ዘ አፍሪካ ሪፖርት፡- በኢትዮጵያ የሚመራው የአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ሰላም አስከባሪ ኃይል (አሚሶም) ጥቃት እንዴት እየሄደ ነው?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- የኢሚሶምና የኢትዮጵያ ወታደሮች ከተቀናጁ በኋላ ሁኔታዎች ተቀይረዋል፡፡ ከኢሚሶም ጋር በመተባበር ከአልሸባብ ቁጥጥር ብዙ ከተሞችንና መንደሮችን ነፃ አውጥተናል፡፡ ይኼ ግን ወታደራዊ ስኬት ብቻ ነው፡፡ ነፃ የወጡ አካባቢዎች በፍጥነት ሰብዓዊ ዕርዳታ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ይኼ የእኛ ጥያቄ ነው፡፡ አንዳንድ ንቅናቄዎች ቢኖሩም በቂ አይደሉም፡፡   

ዘ አፍሪካ ሪፖርት፡- በእነዚህ ጥቃቶች የኢትዮጵያ ወታደሮች በግልጽ መታየት አልሸባብ ኢትዮጵያ ውስጥ የአፀፋ ጥቃት ይፈጽማል የሚል ሥጋት አላሳደረብዎትም?

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፡- ሁሌም የአልሸባብ የጥቃት ዒላማ ሆነን ነው የኖርነው፡፡ ዋናው ነገር የሕዝባችን ጠንቃቃ መሆን ነው፡፡ የደኅንነት ተቋማችንም በንቃት ሥራውን ሊሠራ ይገባል፡፡ ይኼ ደግሞ የዕለት ተዕለት ተግባራችን ነው፡፡ 

 

- EthiopianReporter

 

 

Post your comment

Comments

Be the first to comment

Related Articles