ደረጀ ሕዝቅኤል ብሎታል ያለዉን ማስረጃዉን ማቅረብ አለበት - EIZKEIL GEBISSA

ይህችን አጭር ማስታወሽ የምፀፈው ሰሞኑን ሕዝቅኤል ገቢሳ ብሎዋል ተብሎ በማህበራዊ ሚዲያ የሚንሸራሸር ሀሜት ለማስተባበል አይደለም። ሀሜት ከነስሙ ማስተባበል አይቻልም። ምክንያቱም ሃሜተኛው ደፍሮ ብቅ አይልምና። እስካሁንም ድረስ መልስ ያልሰጠሁት ሀሜትና ውሸት እንዳላከብር ብዬ ነው።

ወዳጆቼና ለኔ በጎ አስተሳሰብ ያላቸው ማንነቴን ከሞላ ጎደል ስለሚያውቁ የቀጣፊ ሰለባ ይሆናሉ ብዬ አልሰጋሁም። ከሩቅ የሚያውቁኝ እንኩዋን የራሳቸውን ዳንኝነት መስጠት ይችላሉ። እየሰጡም ነው። ፈቃደ ሸዋቀና ጀምሮታል። አመሰግነዋለሁ። ለማንኛውም እንኩዋን በሕይወት ያሉ በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች የተማሩ ወንድሞቼና እህቶቼ ይቅሩና ቅደመ አያቴም አማርኛ አቀላጥፈው ይናገሩ ነበር። ይፅፉም ነበር። ፅሁፎቹ አሁንም ድረስ አሉ። እኔ ከቋንቋ ሆነ ከሰዉ ጋር ችግር የለኝም። ከሥርዓት ጋር እንጂ።

እኔን ያስገረመኝ ሃሜተኛው አይደለም። ጋዜጠኞችም በዚህ የቀጣፊ ሠረገላ ተፈናጥተው የሐስት ዘመቻ አራማጆች ሆነው ማየቴ ነው። እንዲህ ከሆነ ይህች ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም ብዬ አስተያየት ለመስጠት ፈለግሁ።

አቶ ደረጀ ሀብተወልድ የኢሳት ጋዜጠኛ ናቸው። ለኔ እንደሚገባኝ ጋዜጠኝነት ሙያ ቢሆንም የሕዝብ ባለአደራነት (public trust) ያለበት ሙያ ነው። ባለሙያው በግል ሕይወቱ እንኩዋን እንደሌላው ሰው ሁሉ የመሰለዉን ሁሉ ማነብነብ አይገባዉም። በግል ጊዜዉም ቢሆን ውሸት እንዳያስተጋባ መጠንቀቅ አለበት። ምክንያቱም የመንደር ወሬ አባራሪ ከሆነ በህዝብ ዘንድ ያለው አመኔታ ይጎድላል። ጋዜጠኛ የሆነዉን በማስረጃ ሳያረጋግጥ በህዝብ ፊት ወጥቶ እንደመጣለት የሚናገር ከሆነ የሙያውን ጠባይ አያውቅም ማለት ነው። ለጋዜጠኝነት የሚመች ስብዕናም ባህርይም የለዉም። የህዝብ ባለአደራ መሆኑን አልተረዳም ማለት ነው። ጋዜጠኛ ሳይሆን ቆርጦ ቀጥል፣ ወሬ አመላላሽ፣ አሉቡዋልተኛ፣ ዉሸት ቸርቻሪ ይሆናል። ይህ ዕውነት ካልሆነ አቶ ደረጀ ሕዝቅኤል ብሎታል ያለዉን ማስረጃዉን ማቅረብ አለበት።

በነግራችን ላይ እኔና አቶ ደረጀ በአየር ላይ እንኩዋን ተገናኝተን አናውቅም። እኔ አቶ ፀጋዬ ገብረመድህንን አቶ ሰሎሞንን ደሬሳ እና አቶ ይልማ ደሬሳ በግሌ ልወቃቸው አልወቃቸው ምንም የሚያውቀው ነገር የለም። የኔን ሃሳብ ይጋሩ አይጋሩ ከነርሱ ጠይቆ የተረዳው ነገር እንደሌለ እኔ በዉል አውቃለሁ።ለማመዛዘን ይረዳው ዘንድ የአቶ ፀጋዬን "አዋሽ" የሚለውን ግጥም ጋብዤዋለሁ። ፀጋዬ ስለወንዝ ነው የገጠመው እንደሚለኝ እርግጠኛ ነኝ። ይህችን መስመር ይዞ ሌላ ክርክር ለመክፈትም ይቃጣው ይሆናል። እርሱን ሌላ ጊዜ። እውነት ካለህ ማስረጃ አቅርብ። ካልሆነ እኔ የኢሳት አስተዳዳሪ ብሆን እንደ ደረጀ ያለ ለእዉነት አክብሮት የሌለውን ጋዜጠኛ ቶሎ ብዬ ነወ የማሰናብተው።

 

Post your comment

Comments

Be the first to comment

Related Articles