የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ እና የአገር አንድነትን “ያገቱት” ሦስት ተፃራሪ ኃይሎች (ዘዉዴ ጉደታ ሙለታ

ከዘዉዴ ጉደታ ሙለታ
ታህሳስ 26 ፤ 2009 ዓ ም

ብዙዎቻችን በየቆምንበት ማዕዘን ላይ ሆነን ስለአገራችን ኢትዮጵያ ትክክለኛ የመሰለንን ሁሉ እንናገራለን፤ የዛሬ ችግሮቻችን ናቸዉ ለምንላቸዉ ጉዳዮችም ትክክለኛ መስለዉ የታዩንን የመፍትሔ ሃሳቦች ለማቅረብ እንሞክራለን:: ጥቂቶች ደግሞ የሚያምኑባቸዉን ጉዳዮች መሠረት በማድረግ አመቺ ሆነዉ ያገኟቸዉን መድረኮች ተጠቅመዉና ጊዜያቸዉንም ሰዉተዉ ማራኪ፣ አስተማሪና አሣማኝ የሆኑ ጽሑፎችን ለአንባቢያን በማቅረብ ጠቃሚ ዉይይቶችን ያስነሳሉ፤ በሚያቀርቧቸዉ ጽሑፎች አማካይነትም አንባቢዎቻቸዉን ያስተምራሉ፤ ከአንባቢዎቻቸዉም ይማራሉ፡፡ ከዚያ ከፍ ባለ ደረጃ የተሰለፉት አገሬን፣ ወገኔንና ነፃነቴን ያሉ ኢትዮጵያዉያን ደግሞ የሚያምኑበትን ዓላማ በሚያራምዱ (እናራምዳለን በሚሉ) የፖለቲካ ድርጅቶች ጥላ ሥር ተሰባስበዉ የየበኩላቸዉን አስተዋፅኦ ለማበርከት ይፍጨረጨራሉ፡፡ ቆራጥ የሆኑት ጥቂቶቹ ደግሞ የተመቻቸ ኑሯቸዉንና የሚወዱትን ቤተሰባቸዉን ትተዉ ትግሉ የሚጠይቀዉን መስዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል በመወሰን በግንባር ቀደምትነት ተሰልፈዉ ታግለዉ በማታገል ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ ምርጥ ኢትዮጵያዉያን ያሉባቸዉን አላስፈላጊ ጫናዎችና ተፅዕኖዎች ሁሉ ተቋቁመዉ የነፃነት ትግሉን በሕዝባዊ ድል ለመደምደም በሚያስችል ደረጃ ለማራመድ ተጨባጭ እርምጃዎችን እየወሰዱም ይገኛሉ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን ወያኔን በመቃወም የሚደረገዉ ትግል ለሚፈለገዉ ዉጤት ሊበቃ አልቻለም፡፡

በመሠረቱ ሃያ-አምስት ዓመታትን ያስቆጠረዉ ወያኔ-መራሹን መንግሥት በመቃወም በየአቅጣጫዉ የሚደረግ ትግል ለምን የተፈለገዉን ግብ መምታት ወይንም ለምን የኢትዮጵያ ሕዝቦች በጉጉት የሚጠብቁትን ዉጤት ማስገኘት እንዳልቻለ ለማወቅ ራሱን የቻለ ሣይንሳዊ ጥናት በቂ ዕዉቀት፣ ጊዜ፣ ልምድ፣ ችሎታና የተሟላ ፍላጎት ባላቸዉ የማህበራዊ ሣይንስ ባለሙያዎች መደረግ ይኖርበታል፡፡ ከሣይንሳዊ ጥናት በመለስ ግን በግልፅ የሚታዩና ብዙዎች በቀላሉ የሚረዷቸዉን ምክንያቶች ማየት ተገቢ ነዉ፡፡ የዚህ ፅሑፍ ዓላማ እነዚህን ነጥቦች በማንሣት “ለገንቢ ዉይይት” መነሻ ሊሆን የሚችል ሃሳብ በግልፅነት፣ በቅንነትና በድፍረት ለማቅረብ መሞከር ይሆናል፡፡

እዚህ ላይ “ገንቢ ዉይይት” ለሚለዉ ሃሣብ (ነጥብ) አንባቢያን ተገቢዉን ትኩረት መስጠት ይኖርባቸዋል፡፡ ምክንያቱም መከባበር ሣይሆን መናናቅ፣ ፍቅር ሣይሆን ጥላቻ፣ እኛ/ለእኛ ሣይሆን እኔ/ለእኔ፣ መቀራረብ ሣይሆን መራራቅ፣ መተባበር ሣይሆን መበታተን፣ መግባባት ሣይሆን መቃቃር፣ መመሰጋገን ሣይሆን መወቃቀስ፣ ወዘተ ጎልተዉ በሚታዩበት የወያኔ ተቃዋሚ ወገኖች የፖለቲካ መስክ በሚገባ ያልታሰበባቸዉን አፍራሽ ሃሳቦች በስሜታዊነት መወርወርና እኛ የማናምንበትን ሃሳብ ይዞ የተነሣን ወገን ማሳነስ፣ ማዋረድና ማሸማቀቅ እየተለመደ የመጣ የዘወትር ተግባር ስለሆነ ነዉ፡፡ ይህ ድምዳሜ ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ በየድህረ-ገጹም ሆነ በማህበራዊ መገናኛ መድረኮች፣ በተለይም በፌስ-ቡክ የሚወጡ ጽሑፎችንና በጽሑፎች ላይ የሚሰጡ የአንባቢያን አስተያየቶችን ማየት ይበቃል፡፡ ስለሆነም የሕዝቦቻችን መከራና ስቃይ አሁን በደረሰበት ደረጃ ላይ ሆነን ስናስብ በተለያዩ አገሮች ከምንገኘዉ ኢትዮጵያዉያን መካከል አብዛኞቻችን የሚፈለግብንን፣ የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የዕዉቀት፣ የሞራል፣ ወዘተ አስተዋፅኦዎችን ማበርከታችን ሣይቀር፤ አገር ቤት ያሉት ወገኖቻችን ደግሞ ማመን በሚያስቸግር ሁኔታ ከጨካኝ የወያኔ የአንድ ወገን ሠራዊት ፊት ባዶ እጃቸዉን በድፍረትና በጀግንነት ቆመዉ የአካል፣ የደም ብሎም የሕይወት መስዋዕትነት መክፈላቸዉ ሳይቀር “የፀረ-ወያኔ ተቃዉሞ ትግላችን

ዉጤታማ ያልሆነዉ ለምንድነዉ?” ብለን በግልፅ አለመጠያየቁ ወያኔ-ሠራሽ መከራችንን አርዝሞታል፤ አሁንም ይህንን ጥያቄ ለመጠያየቅ ድፍረቱና ፍላጎቱ ከሌለን የእስከዛሬዉ ዉጤት-አልባ አካሄዳችን መከራችንን የበለጠ ያረዝመዋል፡፡

የፀረ-ወያኔ ትግላችን የሚፈለገዉን ዉጤት አለማስገኘቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ግን ሁሉም የወያኔ ታቃዋሚ ኃይሎች ስለ ሁለት ጉዳዮች ደግመዉ
ደጋግመዉ ያነሣሉ፡-
1. ስለኢትዮጵያ አንድነት – (አንድነትን በመደገፍም በመቃወምም የሚታገሉ ወገኖች መኖራቸዉ እንደተጠበቀ ሆኖ)
2. ስለወገኖቻችን በወያኔ አገዛዝ ሥር የስቃይ ኑሮን ለመምራት መገደድና ከዚህ አስከፊ ኑሮ ነፃ ለመዉጣት መታገል አስፈላጊ ስለመሆኑ፡፡
እነዚህ ሁለት ጉዳዮች ዕዉነትም የሚያነጋግሩና ትኩረት ሊሰጣቸዉ የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸዉ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ለጥያቄዎቹ እስከአሁን አጥጋቢ መልስ ለማግኘት ያልተቻለበት ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ አለመሞከር ለወደፊቱም ወያኔ-ሠራሽ መከራችንን እንደሚያረዝመዉ አያጠያይቅም፡፡ ስለሆነም ነገ ሣይሆን ዛሬ፣ በመሸፋፈንና በማድበስበስ ሣይሆን በግልፅነት፣ በሚያራርቅና በሚያቃቅር መንገድ ሣይሆን በሚያቀራርብና በሚያግባባ መንገድ፣ ለጥርጣሬ በር በሚከፍት መንገድ ሣይሆን መተማመንን መፍጠር በሚያስችል መልኩ አንዳንድ መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን በድፍረት አንስተን ልንወያይባቸዉ ይገባል፡፡ ይህን ካደረግን ወያኔን ተባብረን መጣልና ከወያኔ ዉድቀትም በኋላ አገራችንን ለሁላችንም ልትስማማና ሁላችንንም እንደልጆቿ በእኩልነት ልታቅፈን በምትችልበት መንገድ የመገንባቱ ሥራ ከባድ አይሆንም፡፡

በዚህ ረገድ በቅርቡ የተመሠረተዉ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ (Ethiopian National Movement) እስከአሁን በተቃዉሞዉ ጎራ ሲታዩ የነበሩትን ድክመቶች አስወግዶ፣ ችግሮችን በተቻለ መጠን ፈትቶና ካለፉት ስህተቶች ትምህርት ወስዶ ለሁሉም ልጆቿ የምትመች ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን በጠንካራ ሕዝባዊ መሠረት ላይ እንደአዲስ ለመመሥረት የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት እርምጃዎችን ይወስዳል ተብሎ ይታመናል፡፡ ሕብረ-ብሔራዊ በሆነና ብሔር-ብሔረሰቦችን መሠረት አድርገዉ በተደራጁ አራት የፖለቲካ ኃይሎች የጋራ ስምምነት የተመሠረተዉና ሌሎች ዲሞክራሲያዊ ኃይሎችንም ለማካተት በሩ ክፍት መሆኑን በማያሻማ ቋንቋ አስቀምጦ ሥራዉን በይፋ የጀመረዉ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ የኢትዮጵያን ሕዝቦች የነፃነት ትግል ከፍ ወዳለ ደረጃ ላይ ለማድረስና በተበታተነ መንገድ እየተካሄደ ያለዉን የነፃነት ትግል አቀናጅቶ በሕዝባዊ ድል ለመደምደም የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ለማመቻቸት በሚያስችለዉ ጎዳና ላይ ለመራመድ ወስኖ ለመነሣቱ የንቅናቄዉ መሪዎች በተለያዩ መድረኮች ላይ ከሰጧቸዉ ይፋዊ መግለጫዎች በተጨማሪ በግልፅ ቋንቋ የተቀመጠዉ የንቅናቄዉ መጠሪያ ስም ራሱ በቂ ምስክር ነዉ፡፡ ስሙ በግልፅ እንደሚያመለክተዉ ንቅናቄዉ “አገራዊ”ነዉ፤ ያቺ አገር ደግሞ ወደድንም ጠላንም የሁላችንም የጋራ ቤት የሆነችዉ “ኢትዮጵያ”ናት፡፡ ስለሆነም ራሣቸዉን “የአንድነት ኃይሎች” ብለዉ የሚጠሩ ወገኖች ጧት ማታ እንደዋነኛ የመታገያ አጀንዳቸዉ አድርገዉ የሚያቀርቡትና ለብሔር-ብሔረሰቦች መብት መከበር እንታገላለን የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎችንና ልሂቃንን በአገር አፍራሽነት ወይንም በፀረ-አንድነት የሚከሱበት “የአገር አንድነት”ጉዳይ የሁሉም ሕዝቦች መሠረታዊ የዲሞክራሲ መብቶች ሣይሸራረፉ እስከተከበሩ ድረስ በኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ መሥራቾች ዘንድ ለጥያቄ የሚቀርብ ጉደይ አይደለም፡፡ የሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች ፍላጎት ከግምት ዉስጥ ገብቶ ያልተሸራረፈ የዲሞክራሲ መብትን ዕዉን ማድረግ እስከተቻለ ድረስ“የአገር አንድነት”ጉዳይ አሣሣቢ አይሆንም የሚል ጠንካራ እምነት ባይኖር ኖሮ ከመጀመሪያዉም አገራዊ ንቅናቄዉ ባልተመሠረተ ነበር፡፡

የኢትየጵያ አገራዊ ንቅናቄ መሥራቾች ስለንቅናቄዉ ምሥረታዉ ይፋ ባደረጉበት ሰነድ (declaration) ላይ በግልፅ እንዳስቀመጡት የንቅናቄዉ “ራዕይ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት የሚጠበቅበት፤ የአገሪቱ ብሔር ብሔረሰቦች መብት ሳይሸራረፍ የሚከበርበት፤ ባህላቸዉ፣ ታሪካቸዉና ማህበራዊ እሴቶቻቸዉ የሚንፀባረቁበት፤ ሁሉም የአገሪቱ ሕዝቦች በዜግነታቸዉ ተከብረዉ በህግ ፊት በእኩልነት የሚስተናገዱበት እና ዕድገትና ብልፅግና የሰፈነበት ዲሞክራሲያዊ የሆነ የፌዴራል ሥርዓት መመሥረት ነዉ፡፡ … የንቅናቄዉ ተልዕኮ ደግሞ ሁሉንም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አስተባብሮ በአንድ አገራዊ ዓላማ ሥር በማሰባሰብ ከሕዝቦች ፍላጎት ዉጭ በጠመንጃ ኃይል የያዘዉን ሥልጣን በመጠቀም የአገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ወታደራዊ ተቋማት በበላይነትና በብቸኝነት የተቆጣጠረዉን አምባገነን ሥርዓት በተባበረ ሕዝባዊና ነፍጥ-አልባ ትግል አስወግዶ ዕዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ የፌዴራል ሥርዓት መመሥረት የሚለዉን የአገራዊ ንቅናቄዉን ራዕይ ከግብ ማድረስ ይሆናል፡፡” እንግዲህ ከዚህ ራዕይና ተልዕኮ በግልፅ የምንረዳዉ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ የተመሠረተዉ በወያኔ መዳፍ ሥር ያለችዉን የዛሬዋን ኢትዮጵያ በተባበረ ትግል ከወያኔ የጭቆናና የአፈና ቀንበር የማላቀቅ ፍላጎትና ዓላማ ብቻ ባላቸዉ ደርጅቶች ሣይሆን የነገዋ ድህረ-ወያኔ ኢትዮጵያ ህልዉናም በጣም በሚያሣሰባቸዉ ኃይሎች የመሆኑን እዉነታ ነዉ፡፡

በመሠረቱ ስለኢትዮጵያ የዘመናት ችግሮች ስናስብ እና ሕዝባችን ብሶቱ ገንፍሎ እስከአፍንጫዉ ድረስ የታጠቀዉን የወያኔ ሠራዊት በባዶ እጁ መጋፈጡንና ጥሎም እየወደቀ መሆኑን ስናይ አሣሣቢዉ ነገር የወያኔ መዉደቅ አይደለም፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነዉ እንጂ አምባገነኑ የወያኔ ሥርዓት በሕዝቦች የተቀናጀ ትግልና በተከተለዉ የጥፋት መንገድ ምክንያት አንድ ቀን መዉደቁ አይቀሬ ነዉ፡፡ ሊታሰብበት የሚገባዉና የሁሉንም ባለድርሻ ወገኖች ትኩረት (the serious attention of all stakeholders) የሚሻዉ ዋና ጥያቄ “ከወያኔ መዉደቅ በኋላ የምትኖረዉ ኢትዮጵያ ምን ዓይነት ኢትዮጵያ ትሆናለች?”የሚለዉ ነዉ፡፡ ያቺ የነገዪቷ ድህረ-ወያኔ ኢትዮጵያ እንደ ቅድመ-ወያኔዋና በወያኔ የግፍ፣ የጭካኔ፣ የመሃይምነትና የራስ ወዳድነት ጫማ ሥር ስትረገጥ እንደነበረችዋ ኢትዮጵያ ለጥቂቶች ተንከባካቢ እናት፤ ለአብዛኛዎቹ ልጆቿ ግን ከጨካኝ የእንጀራ እናትም የባሰች ጨካኝ ሆና ትቀጥላለች? በሌላ አባባል ድህረ-ወያኔ እንደ አዲስ የምትገነባዉ ኢትዮጵያ በየትም ብለዉ ሥልጣን ለመያዝ የቻሉ ጥቂት ወገኖች ከመጠን በላይ ተደስተዉና ተንደላቀዉ የሚኖሩባት፤ ወያኔዎች ሲያደርጉት እንደነበረዉና አሁንም እያደረጉ እንዳሉት ጥቂት ባለጊዜዎች ብቻ እንደልባቸዉ የሚዘርፏት ፣ አብዛኞቹ የአገሪቱ ዜጎች ግን የሚራቡባት፣ የሚታረዙባት፣ ለጥቂቶች ብልፅግና ሲባል ብዙሃን ቤትና ንብረት አልባ የሚደረጉባት፣ ከዚያም አልፎ ሰላማዊ ዜጎቿ በሰላም ወጥተዉ ስለመግባታቸዉ እርግጠኞች የማይሆኑባት የችግርና የስቃይ ተምሳሌት እንደሆነች ትቀጥላለች? እነዚህ ጥያቄዎች ፍትህን፣ ነፃነትን፣ እኩልነትንና ያልተሸራረፈ የዲሞክራሲ መብት መከበርን በሚፈልግ በእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መመለስ ያለባቸዉ ጥያቄዎች ናቸዉ፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምንሰጣቸዉ መልሶች የእስከዛሬ አካሄዶቻችንን ዞር ብለን እንድናይ ሊያደርጉን ስለሚችሉና ስህተቶች ከነበሩም ከስህተቶቻችን እንድንማር ስለሚያደርጉን የተቃዉሞ ትግሉን ወደፊት ለማራመድ መንገድ ከፋች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

ስለሆነም በወያኔ የግፍ አገዛዝ ሥር ያለችዉ የዛሬዋ ኢትዮጵያና የሚፈልጉትን ዓይነት መንግሥታዊ ሥርዓት ለማግኘት ያልታደሉት የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሁኔታ የሚያስብ አዕምሮ ያለዉን ታዛቢ በጣም የሚያሣዝኑ ከመሆንም አልፈዉ የሕዝቦቻችንና የአገራችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ እጅግ አሣሣቢ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነዉ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ እስከአሁን ያየናቸዉ የወያኔ ሥርዓት ቁንጮዎች የፈፀሟቸዉና ዛሬም የሚፈፅሟቸዉ የግፍ ድርጊቶች እንኳንስ በመንግሥትነት ስም እናስተዳድረዋለን በሚሉት የራስ ሕዝብ ላይ ቀርቶ በወራሪነት በተቆጣጠሩት ባዕድ ሕዝብ ላይ እንኳን ተፈፅመዋል ሲባል የሰማናቸዉ አይደሉም፡፡ በዚህ ረገድ አገራችንን በግፍ ወርሮ የነበረዉና በቀደምት አባቶቻችን የአንገዛም ባይነት ትግል የሃፍረት ማቅ ተከናንቦ የተባረረዉ የሞሶሎኒ ፋሺስት መንግሥት እንኳን የዛሬዎቹ የሕወሐት ገዢዎች ያደረጉትንና የሚያደርጉትን ዓይነት ለሰሚ ጆሮ የሚዘገንን ግፍ በኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ አልፈፀመም፡፡

የህወሐት ገዢ ቡድን ወላጅ እናትን በጭካኔ በገደለዉ ልጇ ሬሣ ላይ አስቀምጦ ለሌሎች እናቶች መቀጣጫ እንድትሆን ያደረገ፣ በተለያዩ የፈጠራ ወንጀሎች አሳብቦ በቁጥጥሩ ሥር ያዋላቸዉን ሰዎች በጥይት ፈጅቶ ለማስመሰል የታጎሩበትን እስር ቤት በዉስጡ ካሉት እስረኞች ጋር በእሳት ያቃጠለ፣ ባዶ እጁን የዕምነት በዓሉን ለማክበር የተሰበሰበንና ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተቃዉሞዉን ለመግለፅ የሞከረን ሕዝብ በምድር እስከአፍንጫዉ በታጠቀ የወታደር ኃይል ከሰማይ ደግሞ የመርዝ ጭስ በሚረጩ የጦር ሄሊኮፕተሮች አስገድዶ/አፍኖ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ገደል ዉስጥ ገብተዉ እንዲያልቁ ያደረገ ለግፈኛነቱ ተወዳዳሪ የማይገኝለት የወሮበሎች ቡድን ነዉ፡፡ የሥርዓቱ ተቃዋሚ የሆንን ወገኖች ደግሞ የሕወሐት ገዢ ቡድን ይህን ሁሉ ግፍ በሕዝባችን ላይ ማድረሱንና አሁንም እያደረሰ መሆኑን እያየንና እየሰማን ተባብረን ከሕዝባችን ጫንቃ ላይ እንዲወርድ ለማድረግ የሚያስችለንን ትግል እንደማጠናከር ለጥቃቅን ልዩነቶች ቅድሚያ በመስጠት ዕዉነተኛዉን ጠላት ረስተን እርስ በርሳችን በጠላትነት መተያየትን የዘወትር ተግባራችን አድርገነዋል፡፡

ተባብሮ ፋይዳ ያለዉ ሥራ መሥራት የማይችለዉን የተቃዋሚ ጎራ ከምንጊዜዉም በላይ የናቀዉ የሕወሐት ቡድን በሕዝቡ ላይ የሚወስደዉን የግፍና የንቀት እርምጃ ከጊዜ ወደጊዜ እየቀያየረ “እስቲ ምን ታመጣላችሁ?” እያለን ነዉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ከሰሞኑ የንቀት ድርጊቱ የበለጠ ማረጋገጫ የለም፡፡ ሰሞኑን ከራሱ የዜና አዉታሮች እንደሰማነዉ “የኢትዮጵያ መንግሥት” ተብዬዉ ሕወሐት-መራሽ የጥቂቶች ቡድን በጭካኔ በትር አንቀጥቅጦ ከሚገዛቸዉ የአገሪቱ ዜጎች መካከል በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩትን በእስረኝነት ስም አፍኖ በየማጎሪያ ማዕከላቱ ሲያሰቃይ (torture ሲያደርግ) ከከረመና አንዳንዶቹንም አካለ ጎደሎ ካደረገ በኋላ ሲለቃቸዉ ነፃ የእስኮላርሺፕ ዕድል በመስጠት ዩኒቨርሲቲ አስገብቶ በማስተማር ያስመረቃቸዉ ይመስል “ሥልጠና ሰጥቼ አስመርቄያለሁ” ብሎ በማወጅ በግፍ አንቀጥቅጦ በሚገዛቸዉ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ላይ መቀለዱን ታዝበናል፡፡ ይሉኝታ ቢሱ የወያኔ መንግሥት ተብዬ ቡድን በእንደዚህ ዓይነቱ የማላገጥ ተግባር በዓለም ላይ ተወዳዳሪ የማይገኝለት “ልዩ ልማታዊ መንግሥት” መሆኑንም አስመስክሯል፡፡ እዉነታዉ ግን እነዚህ መብታቸዉን በሰላማዊ መንገድ ለመጠየቅ ከመሞከር ዉጭ ምንም ወንጀል ያልሠሩ ንፁሃን ዜጎች ታስረዉ በቆዩበት ወቅት ከበቂ በላይ ግፍ የተፈፀመባቸዉና ለሌሎች ተረኛ ታፋኞች ቦታ እንዲለቁ ለማድረግ ታስቦ ከጠባቡ እስር ቤት ወጥተዉ ሰፊ ወደሆነዉ የወያኔ እስር ቤት መዛወራቸዉ ነዉ፡፡ ምክንያቱም በወያኔ አገዛዝ ሥር ያለችዉ አገራችን ኢትዮጵያ የመቃወም፣ የመደራጀት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ፣ ወዘተ መብቶች የሌሉባት ሰፊ እስር ቤት ናትና፡፡ ስለሆነም ይህ እስረኞች የነበሩ ዜጎችን “የተሃድሶ ሥልጠና ሰጥቼ አስመርቄያለሁ” የሚለዉ የወያኔ ዜና ቡድኑ ለኢትዮጵያ ሕዝቦች ያለዉን ወደር የለሽ ንቀት በድጋሚ ያረጋገጠበት ነዉ ከማለት ዉጭ ሌላ ትርጉም የሚሰጠዉ አይደለም፡፡

እነዚህን “የተሰጣቸዉን ሥልጠና ጨርሰዉ የተመረቁ” የግፍ ታሣሪዎችን በተመለከተ “የኢትዮጵያ ብሮድካስቲነግ ኮርፖሬሽን (EBC)”
በሚባለዉ የሥርዓቱ የዉሸት ዜናዎች ማምረቻ ተቋም አማካይነት በተሠራጨዉ ዜና ዉስጥ የሚከተለዉ ይገኝበታል፡-

“በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ኮማንድ ፖስት አፈፃፀም መመሪያ መሰረት በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ዜጎች የተሃድሶ ስልጠና መውሰዳቸው በቀጣይ ህዝብን ለመካስ ዕድል እንደሚሰጣቸው የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ገለፀ፡፡በተሳሳተ መረጃ እንዲሁም በስሜት ተገፋፍተው በሁከት የተሳተፉ ወጣቶች ወደቀድሞ ሰላማዊ ህይወት እንዲመለሱ የተሰጠው ስልጠና ጠቃሚ ነበር፡፡ በተሃድሶው የተሳተፉት ስልጣኞች በእጅጉ መፀፀታቸው አይደገምም የሚል መፈክር በማንገብ ድርጊቱን አጥብቀው ማውገዛቸውን ገልጿል፡፡ በኮማንድ ፖስት የአፈጻጸም መመሪያ መሰረት በወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የሚውሉ ዜጎች እንደ ወንጀላቸው ተለይተው ቀለል ያለ ወንጀል የፈጸሙት ስልጠና ወስደው ሲለቀቁ ከባድ ወንጀል ፈጽመው የተገኙት ደግሞ በህግ አግባብ እንደሚጠየቁም ገልጿል።

ጽህፈት ቤቱ በሃገሪቱ በተወሰኑ አካባቢዎች በተፈጠሩ ሁከቶችና ብጥብጦች የተነሳ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር ከዋሉት ዜጎች መካከል 9ሺህ 800 ያህሉ የተሃድሶ ስልጠና አጠናቀው እና ተመርቀው ሰሞኑን ወደ ህብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ መደረጋቸውን አስታውሷል። አብዛኛዎቹ የሁከቱ ተሳታፊዎች ወጣቶች መሆናቸው የጠቀሰው መግለጫው በተቀነባበረ ቅስቀሳ እና በተሳሳተ መረጃ እንዲሁም በስሜት ተገፋፍተው ወደ ሁከት መግባታቸውን እንስተዋል። ወጣቶቹ ወደቀድሞው ሰላማዊ ህይወታቸው በመመለስ የልማቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ ስልጠና ወስደው መመረቃቸው አስፈላጊና ጠቃሚ እርምጃ መሆኑን መንግሥት ያምናል ብሏል መግለጫው።”

እንደዚህ የሚያላግጥብንን የአረመኔዎች ሥርዓት እንቃወማለን የምንል ወገኖች ይህ ሁሉ ተሰምቶም ታይቶም የማይታወቅ ግፍ በሕዝቦቻችን ላይ ተፈፅሞ እያየንና እየሰማን ተባብረን በየአቅጣጫዉ በተለያዩ መንገዶች እየተካሄዱ ያሉትን የአልገዛም ባይነት እንቅስቃሴዎች በሚገባ አጠናክረን አገራችንንና ሕዝቦቻችንን ከዚህ የኢትዮጵያዉያን ደመኛ ጠላት ከሆነ ቡድን እጅ እንዴት ነፃ ልናወጣ እንደምንችል በቅንነት፣ በንፁህ ልቦና እና በግልፅነት እንደመመካከር ጎራ ለይተን መናከስን የዘወትር ተግባራችን አድርገናል፡፡ አሁን አሁንማ የለየለት ጠላታችን የሆነዉ የሕወሐት የገዢ ቡድን ተረስቶ አንዳንዶቻችን በየጽሑፎቻችንም ሆነ በየንግግሮቻችን ዘወትር የምናወግዘዉ የአንዳንድ ፖለቲካ ድርጅቶችን መሪዎችና በወያኔ ተቃዋሚነት የሚታወቁ ግለሰቦችን ሆኗል፡፡

እንደዚህ የሚያላግጥብንን የአረመኔዎች ሥርዓት እንቃወማለን የምንል ወገኖች ይህ ሁሉ ተሰምቶም ታይቶም የማይታወቅ ግፍ በሕዝቦቻችን ላይ ተፈፅሞ እያየንና እየሰማን ተባብረን በየአቅጣጫዉ በተለያዩ መንገዶች እየተካሄዱ ያሉትን የአልገዛም ባይነት እንቅስቃሴዎች በሚገባ አጠናክረን አገራችንንና ሕዝቦቻችንን ከዚህ የኢትዮጵያዉያን ደመኛ ጠላት ከሆነ ቡድን እጅ እንዴት ነፃ ልናወጣ እንደምንችል በቅንነት፣ በንፁህ ልቦና እና በግልፅነት እንደመመካከር ጎራ ለይተን መናከስን የዘወትር ተግባራችን አድርገናል፡፡ አሁን አሁንማ የለየለት ጠላታችን የሆነዉ የሕወሐት የገዢ ቡድን ተረስቶ አንዳንዶቻችን በየጽሑፎቻችንም ሆነ በየንግግሮቻችን ዘወትር የምናወግዘዉ የአንዳንድ ፖለቲካ ድርጅቶችን መሪዎችና በወያኔ ተቃዋሚነት የሚታወቁ ግለሰቦችን ሆኗል፡፡

በተለይም የእስከዛሬዉ የተናጠል የተቃዉሞ ትግል የምንፈልገዉን ዉጤት አላመጣምና ተባብረን የጋራ አገራችንንና ሕዝቦቻችንን ከሕወሐት አገዛዝ ነፃ እናዉጣ ብለዉ በድፍረት የተነሱትንና የጋራ የሆነ አገራዊ ንቅናቄ መመሥረታቸዉን ይፋ ያደረጉ ድርጅቶችን ታዋቂ፣ ደፋርና ቆራጥ መሪዎች መወንጀል፣ ማንቋሸሽ፣ ባልተጣራ ጥፋት መወንጀል፣ በአጠቃላይ በቀና ጥረቶቻቸዉ ላይ ለጊዜዉም ቢሆን ዕንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ የቃላት ጋሬጣዎችን ማስቀመጥን የዘወትር ተግባራችን አድርገናል፡፡ ሌሎቻችን ደግሞ ያንኑ የተለመደዉንና ከዓመት ወደዓመት የማይቀየረዉን በአንድ በኩል “አንድነት አንድነት” በሌላዉ ወገን ደግሞ “መገንጠል መገንጠል” የሚሉና ቅንጣት ያህል እንኳን ወደፊት ለመራመድ የማያስችሉ ባዶ መፈክሮቻችንን አንግበን በየራሣችን ሙዚቃዎች ብቻችንን ወይንም ጥቂት መሰሎቻችንን አስከትለን የመደነሱን ዉጤት-አልባ ተግባራት ተያይዘናል፡፡

እዚህ ላይ በመካከላችን ያለዉ የብሔረሰብ ልዩነት ሣያግደን ከቅርብ ጓደኛዬ ጋር (ጓደኛዬ የአማራ ብሔር ተወላጅ ነዉ) ወቅታዊዉን የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንስተን በግልፅነትና በመግባባት መንፈስ ስንነጋገር ጓደኛዬ ያነሣዉን ነጥብ እና እኔም ከልብ የማምንበትን እዉነታ ለዚህ ጽሑፍ አንባቢያን ለማካፈል እወዳለሁ፡፡ በዚህ ጓደኛዬ አባባል የኢትዮጵያን የፖለቲካ ሁኔታ በጥልቀት የገመገመ ሰዉ በቀላሉ የሚረዳዉ ዕዉነታ የኢትዮጵያ አንድነት ጉዳይ በሦስት ተፃራሪ ኃይሎች ዕገታ ሥር ያለ መሆኑን ነዉ፡፡ እነሱም፡-
1. ራሣቸዉን “የኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች” ብለዉ የሚጠሩ
2. የመገንጠል አጀንዳን የሚያራምዱ
3. የሕወሐት ገዢ ቡድን ናቸዉ፡፡

 

እስቲ እነዚህ ሦስት ተፃራሪ ኃይሎች የኢትዮዽያን አንድነት እንዴት እንዳገቱ አንድ በአንድ እንይ፦

1. “የኢትዮጵያ አንድነት ኃይሎች”

እስከዛሬ እንደ አንድ አገር ዜጎች በእኩል ሚዛን የምንታይና የሕዝብ ለሕዝብ አንድነት የነበረን ይመስል ለዘመናት የዘለቁና ጠንካራ መሠረት ያበጁ ፍትሃዊ የሆኑ የነፃነት፣ የእኩልነትና የማንነት ጥያቄዎችን ሁሉ ዋጋ በማሣጣት ዘወትር “አንድነት! አንድነት! አንድነት!” ሲሉ የሚደመጡ ወገኖች በዚህ ምድብ ሥር የሚታዩ ናቸዉ፡፡ የአገራችንን የትናንት ታሪክም ሆነ የዛሬ እዉነታ ያለገናዘቡትና ለማገናዘብም የማይፈልጉት እነዚህ ወገኖች አርቆ አሳቢ በመሆን ልዩነቶቻችን እንደተጠበቁ ሆነዉ አብሮነትን “unity within diversity” ማምጣት የሚቻልበትን መንገድ እንደመፈለግ ላለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት ሲያደርጉት እንደነበረዉ ሁሉ ዛሬም “አንድ ሕዝብ፣ አንድ ቋንቋ፣ ወዘተ” የሚለዉን ባዶ መፈክር ጮክ ብለዉ የማሰማቱን ነገር ቀጥለዉበታል፡፡

በዚህ ጽሑፍ አማካይነት እንግዲህ ብዙዎች ለፖለቲካ ትክክለኝነት ሲሉ (for the sake of political correctness) የማያነሷቸዉን ነገር ግን መነሣታቸዉ ይጠቅም እንደሆነ እንጂ በምንም ዓይነት መንገድ ትግሉን የማይጎዳዉን “አንድነትን” የሚመለከቱ መሠረታዊ ጥያቄዎች ለማንሣት እሞክራለሁ፡፡ እንደእኔ እምነት በግልፅነት መነሣትና ራሣቸዉን “የአንድነት ኃይሎች” ብለዉ ከሚጠሩ ወገኖች አጥጋቢ መልስ ማግኘት ከሚገባቸዉ ጥያቄዎች መካከል፡ –
• የኢትዮጵያ አንድነት ስንል ምን ማለታችን ነዉ?
• በአገር አንድነትና በሕዝቦች እዉነተኛ አንድነት መካከል ያለዉን ልዩነትና አንድነት እንዴት እናየዋለን?
• ጭንቀታችን መሆን ያለበት ስለመልከዓ ምድር አንድነት ነዉ? ወይስ ሕዝቦቻችን በመተሣሰብ፣ በመፈቃቀር፣ በመቀራረብ እና በዕዉነተኛ የወንድማማችነት ስሜት ተከባብሮና ተፈቃቅሮ አብሮ መኖር ስለመቻላቸዉ ነዉ?
• እዉነተኛ የሆነ የሕዝቦች አንድነት በኢትዮጵያ ምድር ትላንትና ነበረ? ዛሬስ አለ?
• በየመድረኩ ላይ “አንድነት አንድነት” ስንል የእያንዳንዱ የአገራችን ሕዝብ ማንነት፣ ባህል፣ ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ወዘተ የሚገባዉን ዓይነት ዕዉቅና ባላገኘበትና በሚገባ ባልተከበረበት ሁኔታ በጭፍን እና በመሣሪያ ኃይል የሚመጣ እና በመሣሪያ ኃይል ተጠብቆ የሚኖር አንድነት እስከዛሬ ያስከተለዉንና ለወደፊቱም ሊያስከትል የሚችለዉን ጉዳት አመዛዝነናል?
• ዕዉን ኢትዮጵያዊነት ከብሔር/ብሔረሰብ ማንነታችን ጋር የሚጋጭ የዜግነት መገለጫ ነዉ?
• እዉነተኛ የሕዝቦች አንድነት፣ መተባበር፣ መከባበር፣ መተሣሰብ እና እኩልነት የሰፈነበት የሕዝብ ለሕዝብ አንድነት ለማምጣት ምን ማድረግ አለብን?

እነዚህንና ሌሎችንም መሰል መሠረታዊ ጥያቄዎች ከግምት ባላስገባና በአጥጋቢ መንገድ ባልመለሰ ሁኔታ በየመድረኩ ላይና ባገኘነዉ አጋጣሚ ሁሉ የምናነሣዉ “አንድነት! አንድነት!” የሚል ባዶ መፈክር የምንፈልገዉን “አንድነት” ዕዉን እንድናደርግ የሚያስችለን አይደለም፡፡ በዚህ መፈክር ሥር “አንድነት” ማምጣት የሚቻል ቢሆን ኖሮ ላለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት እጅግ በጣም ጥቂት የሆኑ ጭፍንና አረመኔ ግለሰቦች አገራችንን እንደ የግል ንብረታቸዉ፣ ሕዝቦቻችንንም በዘር ለያይተዉ በባርነት አፍነዉ ባልተጫወቱባቸዉ ነበር፡፡ ይህን ሁሉ እያዩ ግን “የአንድነት ኃይሎች” ዛሬም ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ “አንድነት” የሚለዉን አካሄዳቸዉን አላሻሻሉም፡፡ ማለትም ለሃያ-አምሥት ዓመታት የብሔር-ብሔረሰብ ነፃነት፣ “የፌዴራል ሥርዓት” (fake ቢሆንም) እና ራስን በራስ የማስተዳደር የዉሸት ፕሮፓጋንዳ በወያኔ ሲራገብ በነበረበት ሁኔታ ዉስጥ ሆነን መፈክራችንን እንኳን
“ተጨቁነን ኖረናል አሁንም እየተጨቆንን ነዉ፤” የሚሉ ወገኖችን ሊያካትት በሚችል መልኩ ለማሻሻል አልሞከርንም፡፡

አሁን አሁን ደግሞ ጥቂቶቹ የዚህ ጎራ ተሰላፊዎች “አንድ ጥየቄ” የሚል አዲስ መፈክርም ጨምረዉ ማሰማት ጀምረዋል፡፡ በአንድ ወቅት “አንድ አገር፣ አንድ ሕዝብ፣ አንድ ቋንቋ፣ አንድ ጥየቄ” ያሉኝ አንድ ትልቅ ሰዉ “ጥያቄያችን አንድ ብቻ ነዉ ወይ? ለመሆኑ ያ አንድ ጥያቄ ደግሞ የትኛዉ ነዉ?” ለሚለዉ ጥያቄዬ የመለሱት መልስ እስከዛሬም ይገርመኛል፡፡ እንደ እሳቸዉ አባባል “አንዱና ብቸኛዉ ጥያቄያችን የወያኔን መንግስት ማስወገድ ነዉ፡፡” ነገር ግን ኢትዮጵያ የሁሉም ሕዝቦቿ የጋራ እናት ሆና እንደ አዲስ እንድትመሠረት ለማድረግ ይቻል ዘንድ መነሣትና አጥጋቢ መልስ ማግኘት ያለባቸዉ ጥያቄዎች በርካታ ናቸዉ፡፡ ዘላቂ ሊሆን የሚችል ትክክለኛ የዲሞክራሲ ሥርዓት ዕዉን ለማድረግ ደግሞ ሁሉም ጥያቄዎች የማያዳግሙና የዚያች አገር ጉዳይ በሚያገባቸዉ ወገኖች ሁሉ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸዉ መልሶች ሊሰጧቸዉ ይገባል፡፡ ሁሉንም የሕዝብ ጥያቄዎች በአጥጋቢ ሁኔታ መመለስ የሚያስችል መንገድ መከተል ካልቻልን የምንሣሣላትና ጧትና ማታ ስለአንድነቷ ብቻ የምንዘምርላት አገር ህልዉና አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡

2. የመገንጠል አጀንዳን የሚያራምዱ ወገኖች

የአንድነት ጉዳይን አጠናክረዉ ከሚያቀነቅኑ ወገኖች በተቃራኒዉ የቆሙትና የኢትዮጵያን አንድነት በዕገታ ከያዙት ሦስት ወገኖች መካከል አንዱ የሆኑት ደግሞ “የአገር አንድነት” የሚለዉን ነገር በፍፁም መስማት የማይፈልጉት ናቸዉ፡፡ በዚህ ጎራ የተሰለፉት ወገኖች ወደድንም ጠላንም ኢትዮጵያ የምትባል አንድ የጋራ አገር ያለን መሆናችንን መቀበል የማይፈልጉ፤ የዛሬዪቷ ኢትዮጵያ የተመሠረተችበት የጉልበትና (የጦርነትና) አንዱ ሌላዉን አሸንፎ የማስገበር መንገድም ቢሆን ሌሎች አገሮች ከተመሠረቱበት ሂደት (the forceful process of state formation) የተለየ አለመሆኑን የማይቀበሉ ናቸዉ፡፡ እነዚህ ወገኖች በጣም ጥቃቅን ልዩነቶችን እጅግ አግዝፈዉ የሚያዩ፣ ለልዩነቶች የተለየ ዋጋና ትኩረት የሚሰጡ፣ ሕዝብንና ገዢ መደቦችን ለያይተዉ ማየት የማይፈልጉና የትናንት ድርጊቶችን ሁሉ ለዛሬ መቃቃር እንደ ምክንያት አድርገዉ በማቅረብ ከአንድነት ይልቅ መለያየትን የችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ አድርገዉ የሚያቀርቡ ወገኖች ናቸዉ፡፡

የብሔር-ብሔረሰቦችን መብት መሠረት አድርገዉ የሚታገሉትና መገንጠልን እንደ መፍትሔ አድርገዉ የሚያዩት እነዚህ ኃይሎች የትኞቹም የዓለማችን አገራት (ዛሬ በሥልጣኔም ሆነ በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በጣም ርቀዉ ሄደዋል የሚባሉትን እንደ አሜሪካ ያሉትን አገሮች ጨምሮ) ትናንት ያለፉባቸዉ የመንግሥት ምሥረታ ሂደቶች በጦርነት ላይ የተመሠረቱ እንደነበሩና አሸናፊዉ ተሸናፊዉን በማስገበር መሆኑን ማሰብ ይኖርባቸዋል፡፡ ስለሆነም በተከታታይ የገዢ መደቦች የመረገጥ፣ የመጨቆንና የበታች ተደርጎ የመታየት ችግር የሚፈታዉ በጋራ ትግል አማካይነት የጭቆና ሥርዓትንና ጨቋኞችን በተባበረ ክንድ አስወግዶ እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓትን በመገንባት መሆኑን አምነዉ መቀበል ይኖርባቸዋል፡፡

3. የሕወሐት ገዢ ቡድን

ከሁለቱም ተፃራሪ ጎራዎች ዉጭ የሆነዉና ሁለቱንም ወገኖች እንደ ቀንደኛ ጠላቱ የሚያየዉ የሕወሐት ገዢ ቡድን የመንግሥትነት
ሥልጣኑንና ወታደራዊ ጉልበቱን ተጠቅሞ ለሥልጣን ዕድሜዉ ማራዘሚያ ሁለቱንም ጎራዎች ስልታዊ በሆነ መንገድ ይጠቀምባቸዋል፡፡

3.1 ራሱን የኢትዮጵያ አንድነት ጠበቃ አድርጎ የሚያየዉን ወገን ወያኔ ሥልጣን ላይ ከሌለ የአገሪቱ ዕጣ ፈንታ የመገንጠል አጀንዳን በሚያራምዱት ኃይሎች እጅ በቀላሉ እንደሚወድቅና አገር እንደምትበታተን አምነዉ ለሕወሐት እና ለሕወሐት ብቻ ፀጥ ለጥ ብለዉ እንዲገዙ ለማድረግ ሞክሯል፤ አሁንም እየሞከረ ነዉ፤ በተወሰነ ደረጃም ተሣክቶለታል፡፡

3.2 የነፃነትና የእኩልነት ጥያቄ የሚያነሱትን ወገኖች ደግሞ የእኛ ሥርዓት ከሌለ የተጎናፀፋችሁት ራስን በራስ የማስተዳደር፣ በራስ ቋንቋ የመጠቀምና ሌሎችም ከደርግ መዉደቅ በኋላ የተገኙት “የዲሞክራሲ መብቶች” በነፍጠኛና ትምክህተኛ ኃይሎች ይቀለበሣሉ የሚል አስፈሪ አቀራረብ በመከተል የራሱን የዛሬ የአፈናና የጭቆና አገዛዝ ወደ ጎን በመተዉ የትናንት ጭቆናን ብቻ እንደማስፈራሪያ መሣሪያ ተጠቅሞ የአሁኑ የጭቆናና የዝርፊያ አገዛዙ የሕዝቡን ትኩረት እንዳይስብ ለማድረግ ይጠቀምበታል፤ ተጠቅሞበታልም፡፡ በአጠቃላይ የወያኔ ገዢ ቡድን አንዱን ጎራ የሌላዉ ማስፈራሪያ አድርጎ የሥልጣን ጊዜዉን ለማራዘሚያ የሚጠቀምባቸዉ መሆኑን ባለፉት ዓመታት በተከተለዉ የከፋፍሎ መግዛትና ነጣጥሎ መምታት ፖሊሲዉ በግልፅ አሣይቷል፡፡ እንደሚታወቀዉ የወያኔ ቡድን ዋነኛ ዓላማ ኃላፊነት እንደሚሰማዉ መንግሥት የአገር አንድነት፣ዕድገትና ብልፅግና ወይንም ደግሞ የሕዝቦች ነፃነት፣ እኩልነት፣ ወንድማማችነትና በሰላም አብሮ መኖር የሚረጋገጥበትን መንገድ ማመቻቸት ሣይሆን የትኛዉንም ዘዴ ተጠቅሞ ሥልጣን ላይ በመቆየት ላለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት ያለማቋረጥ ያካሄደዉን የአገርና የሕዝብ ሃብት ዝርፊያ ያለምንም ተቀናቃኝ አጠናክሮ መቀጠል ነዉ፡፡ ለዚህ ዓላማዉ መሣካት ደግሞ በሁለት ተፃራሪ ጫፎች ላይ የቆሙትና እንደ ክፉ ባላንጣ የሚተያዩት ራሳቸዉን “የአንድነትኃይሎች” ብለዉ የሚጠሩትና “የመገንጠልን” ዓላማ የሚያራምዱት ወገኖች በጥሩ መሣሪያነት አገልግለዉታል፡፡
ከላይ በአንደኛና በሁለተኛ ተራ ቁጥር ሥር የተጠቀሱትን የሁለቱንም ኃይሎችም ሆነ የወያኔን ሥርዓት በፍፁም የማይደግፉት በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩት ወገኖች (the silent majority) ደግሞ ለአገሪቱም ሆነ ለሕዝቦቿ ሰላም፣ ደህንነት፣ እኩልነትና አብሮነት የሚበጅ አማካይ መንገድ ተጠናክሮ መዉጣት ባለመቻሉ ከፖለተካዉ ሜዳ ገለልተኛ ሆነዉ መቀመጥን መርጠዋል፡፡

እንግዲህ የተቃዉሞ ትግለችንን ከእነዚህ ሦስት ተፃራሪ ወገኖች ዕገታ ነፃ ማድረግ ካልቻልን ዕጣ ፈንታችን ለሌላ ሩብ ምዕተ ዓመት ወይንም ከዚያም በላይ ለረዘመ ጊዜ በእነዚህ አልጠግብ ባይ ዘረኞች ብሎም በልጆቻቸዉና በልጅ ልጆቻቸዉ ታፍነን መገዛት ይሆናል፡፡ ገዢዎቻችን ደካማ ጎኖቻችንን በሚገባ ስለሚረዱ ተቃዋሚዉ ጎራ የሚራራቅባቸዉንና የሚቃቃርባቸዉን መንገዶች እያመቻቹ ራሳቸዉን የዛሬዎቹ ገዢዎች አድርገዉ ከማስቀመጥም ባሻገር ወጣት ልጆቻቸዉን ከሕዝብ የተዘረፈን ሃብት በመጠቀም በዓለም ላይ ምርጥ ወደሚባሉ የትምህርት ተቋማት በብዛት ልከዉ ለነገ አገር ገዢነት እያዘጋጁ ነዉ፡፡ የአገራችን የአሁኑ ዕዉነታ ይህ ከሆነ እንግዲህ ያለን ዕድል ሁለት ነዉ፡-

1. እስከዛሬም ስናደርግ እንደነበረዉና አሁንም እንደምናደርገዉ ለጥቃቅን ልዩነቶቻችን ከተገቢ በላይ ትኩረት ሰጥተን እየተጋጨን የወያኔን የሥልጣን ዕድሜ ማራዘምና በተገዢነት መቀጠል፤ ወይንም
2. ልዩነቶቻችንን በማያዳግም ሁኔታ ለመፍታት (ለማስወገድ) በሚያስችለን መንገድ የሌላዉንም ወገን ቁስል፣ ህመምና ብሶት ተረድተን እንዲሁም የአንደኛዉን ወገን ስጋትም ከግምት አስገብተን ለሁሉም ወገኖች በሚበጅ አማካይ የሆነ አማራጭ የፖለቲካ መፍትሔ ላይ በመስማማት እጅ ለእጅ ተያይዘን የጋራ ትግላችንን ከምንጊዜዉም የበለጠ በማጠናከር ለዉጤት ማብቃት፡፡

ሁለተኛዉ አማራጭ መንገድ በኢትዮጵያ ጉዳይ ራሳቸዉን ባዕድ አድርገዉ የሚያቀርቡ ወገኖችን የአገር ባለቤትነት እንዲሰማቸዉና በዘመናዊቷ ዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ዉስጥ ራሳቸዉን በግልፅ እንዲያዩ የሚያደርጉ ወሳኝ እርምጃዎችን በድፍረት መዉሰድን ይጠይቃል፡፡ እዚህ ላይ “እነዚህ እርምጃዎች ምንድናቸዉ?” የሚል ጥያቄ በቅንነት ማንሣት ተገቢ ነዉ፡፡ እንደሚታወቀዉ የአገር አንድነት ስጋት ተደርገዉ የሚታዩ ሁኔታዎችን በማንፀባረቅ ከሚታወቁት የአገራችን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች አንዱና የመጀመሪያዉ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ነዉ፡፡ ለዘመናት የዘለቀዉና ዛሬም ድረስ አጥጋቢ መልስ ባለማግኘቱ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች እንደበግ በአደባባይ መታረድ፤ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ የኦሮሞ ልጆች ከአገራቸዉ መሰደድና ቁጥራቸዉን መገመት ለሚያዳግት ንፁሃን ኦሮሞዎች ወያኔ በየሥፍራዉ በከፈታቸዉ የማሰቃያ ማዕከላት ዉስጥ ጭካኔ በተመላበት ሁኔታ መታጎር ምክንያት ሆኗል፡፡

ይህ የተከታታይ የኢትዮጵያ ገዢ ቡድኖች የጭካኔ በትር ያልተለየዉ የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ ፍፁም ልዩ የሆነና ተሰምቶ የማይታወቅ ሣይሆን ማንኛዉም መብቱ የተደፈረ ሕዝብ የሚያነሣዉ የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የፍትህና የዲሞክራሲ መብቶችን መከበር ያካተተ ጥያቄ መሆኑ ከብዙዎች የተሠወረ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ የዚህን ትልቅ ሕዝብ ጥያቄ በቅንነት ተመልክቶ ተገቢ መፍትሔ እንደመስጠት የኦሮሞን ሕዝብ የመሬትና ምድሩ ያፈራዉን አጓጊ የተፈጥሮ ሃብት ያለምንም ከልካይ ለመቀራመት ሲባል ብቻ ተከታታይ ገዢ ቡድኖች የሕዝቡን ጥያቄ በመሣሪያ ኃይል ከማፈንም አልፈዉ ሌሎች የአገሪቱ ሕዝቦች ሣይቀሩ ኦሮሞን የመሰለ ሰላማዊ፣ ደግና የብዙ አኩሪ ባህሎች ባለቤት የሆነ ሕዝብ በአገር ጠላትነት (በአገር አንድነት አፍራሽነት) እንዲፈርጁና ለኦሮሞ ሕዝብ የመብት ጥያቄዎችም የተሣሣተ ትርጉም እንዲሰጡ ለማድረግ ችለዋል፡፡ ስለሆነም እስከዛሬ ድረስ የኦሮሞ ጉዳይ በየትኛዉም መንገድ ሲነሣ በቀጥታ የሚያያዘዉ “ከኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ላይ መዉደቅ” ጋር ነዉ፡፡ ይህን አፍራሽ ሁኔታ ከመሠረቱ መቀየር ካልተቻለና የኦሮሞ ሕዝብ ጥያቄ እንደማንኛዉም ሕዝብ የነፃነት፣ የእኩልነት፣ የሰብዓዊ መብት፣ የፍትህና የዲሞክራሲ ጥያቄ መታየት የሚገባዉ እንጂ “የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ” እንደሆነ ተደርጎ መወሰድ የማይገባዉ መሆኑን መረዳት ካልተቻለ ከምን ገዜዉም በላይ ዛሬ ብዙዎች የሚጓጉለት የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ላይ እንደሚወድቅ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ እዚህ ላይ እንዴት? የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡

ላለፉት ሃያ-አምስት ዓመታት በየትኛዉም የጦር መሣሪያ ጋጋታም ሆነ በእንደ አጋዚ ዓይነቱ የጭካኔ ተምሳሌት በሆነ የወታደር ኃይል ወደኋላ መመለስ በማይቻልበት ሁኔታ በተገነባዉ ጠንካራ የኦሮሞ ማንነት (strong Oromo identity) ምክንያት መብቱ ምንም ሣይሸራረፍ ያልተከበረለትን ኦሮሞ የሆነ የኢትዮጵያ ዜጋ በአጠቃላይ፣ የኦሮሞን ወጣት ደግሞ በተለይ እስከዛሬ ሲደረግ እንደነበረዉ አፍኖ መግዛትና የአሮጌዋ ኢትዮጵያ አካል አድርጎ ለማስቀጠል መሞከር ሁላችንም የምንሣሣላትን አገር እንዳልነበረች ወደማድረግ አስከፊ ደረጃ የሚያደርስ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ይህን ሁኔታ ማስቀረትና የኢትዮጵያን አንድነት በማይነቃነቅ ፅኑ መሠረት ላይ መገንባት የሚቻለዉ ወያኔ ለከፋፍሎ መግዛት ፖሊሲዉ እንዲመች እንዳደረገዉ ዓይነት ማስመሰል የሌለባቸዉን ትክክለኛ ዲሞክራሲያዊ እርምጃዎች በመዉሰድ ነዉ፡፡ ከእነዚህ እርምጃዎች መካከል የኦሮሞን ሕዝብ ቋንቋ (Afaan Oromooን) ከአገሪቱ ኦፊሴላዊ የሥራ ቋንቋዎች መካከል አንዱ ማድረግን፣ “የጎሣ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ አንድነት አስጊ ነዉ” የሚለዉን የትም የማያደርስና ከተጨባጭ ዕዉነታ የራቀ አጉል ፉከራን ትቶ የራስ በራስ አስተዳደር ያለማንም ጣልቃ-ገብነት የሚተገበርበትን እዉነተኛ ፌዴራላዊ ሥርዓት ዕዉን ማድረግንና ለሕዝቡ ታሪክ፣ ባህልና ማህበራዊ እሴቶች ተገቢ ዕዉቅና ብሎም ህገ-መንግሥታዊ ከለላ የሚሰጥ እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባትን እንደ ምሣሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ይህን በጣም አነስተኛ ሊባል የሚችል እርምጃ መዉሰድ ካልተቻለ በብዙ ወገኖች እንደዋነኛ መታገያ አጀንዳ ተደርጎ የሚነሣዉ “የኢትዮጵያ አንድነት” ከምን ጊዜዉም በላይ ለአደጋ የተጋለጠ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ የዚህን አስተሣሰብ ትክክለኛነት ለመረዳት በእያንዳንዱ የኦሮሚያ ዞኖች ተገኝቶ የሕዝቡን ስሜትና አመለካከት በአጠቃላይ የወጣቱን ደግሞ በተለይ ማጥናት ያስፈልጋል፡፡

እንደሚታወቀዉ አገር ቤት ያሉ ወገኖቻችን የጋራ ጠላትን በጋራ የመታገልን አኩሪ ሂደት በተግባር አሣይተዉናል፤ እያሣዩንም ነዉ፡፡ የእኛ ድርሻ መሆን ያለበት ከተራራቁ ጫፎች ወደመሃል መጥተን የወየኔን የገዢነት ዕድሜ ማሣጠርና ወገኖቻችን የጀመሩትን የነፃነት፣ የፍትህ፣ የእኩልነትና የዲሞክራሲ ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ እንዲያገኙ ለማድረግ የበኩላችንን ወሳኝ ሚና መጫወት ነዉ፡፡ ለዚህ ደግሞ የትኛዉንም ዲሞክራሲያዊ ደርጅት፣ ቡድንም ሆነ ስብስብ እንዳማያገል በግልፅ ቋንቋ ያስቀመጠዉና ገና ከመነሻዉ የኢትዮጵያ ጉዳይ ለሚመለከታቸዉ ኃይሎች (Stakeholders) ሁሉ ግልፅ ጥሪ በማድረግ ይፋዊ እንቅስቃሴዉን የጀመረዉ የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ሁሉንም ነፃነት ፈላጊ ወገኖች የሚያሰባስብ አመቺ የጋራ መድረክ ሊሆን ይችላል፡፡ ንቅናቄዉ ዉጤት የሚያመጣ የጋራ መሰባሰቢያ ጥላ (all-inclusive umbrella organization) ሊሆን የሚችለዉ ግን ሁሉም ወገኖች የተናጠል ሩጫቸዉን ትተዉ የእስከዛሬዉ ችግር፣ በደልና ከምንም በላይ ደግሞ የወያኔ መሪዎች ንቀት ከበቂ በላይ ነዉና ሁላችንም ካለፉት ስህተቶቻችን ተምረን በጋራ ዓላማ ሥር እንሰባሰብና ለትክክለኛ እና ዘለቂ መፍትሔ አብረን እንታገል ሲባባሉ ነዉ፡፡

ይህ ቅንነትና አርቆ ማስተዋል የታከለበት ዉሳኔ ብቻ ነዉ በሁለት የተራራቁ ጫፎች የቆሙትን የአገር“አንድነት” ጠበቃ ነን ባይ ወገኖችንም ሆነ ከአብሮነት ይልቅ ልዩነትን የሚያራግቡትን “የመገንጠል” ጥያቄ አራማጆች ማዕከላዊ በሆነ ሥፍራ (middle ground) ላይ እንዲገናኙ በማድረግ በሁለቱ ተፃራሪ ወገኖች መካከል ራሱን እንደአስታራቂ አድርጎ ያቆመዉንና የኢትዮጵያ ሕዝቦች ደመኛ ጠላት መሆኑን ጭካኔ በተመላባቸዉ ድርጊቶቹ ደግሞ ደጋግሞ ያረጋገጠዉን የወያኔ ቡድን ዕርቃናቸዉን ማስቀረት የሚቻለዉ፡፡ ይህን ወሳኝ እርምጃ መዉሰድ ባልተቻለበት ሁኔታ በባዶ ሜዳ “አንድነት! አንድነት!” የሚለዉን መፈክር ጮክ ብሎ ማሰማትም ሆነ “ኢትዮጵያን አፈራርሶ ትንንሽ ነፃ አገሮችን መገንባት” የሚለዉ “የመገንጠል ዓላማ” አራማጆች ሩጫ የሚፈለገዉን አንድነትም ሆነ ነፃ አገር የመመሥረት ህልም ዕዉን ለማድረግ አያስችልም፡፡

ሁለቱም ተፃራሪ አካሄዶች እዉነተኛ የሕዝቦች አንድነት በጠንካራ መሠረት ላይ እንዳይገናባ እንቅፋት የሚሆኑ የአንድነት ፀሮች ከመሆናቸዉም በላይ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በሕዝቦች የተባበረ ክንድ እንዲወርድ የሚፈለገዉ የወያኔ ቡድን ራሱን የሁለቱ ተፃራሪ ጎራዎች አማራጭ አድርጎ በማቅረብ ሥልጣን ላይ ተደላድሎ እንዲቆይ ለማድረግ አመቺ ሁኔታን የሚፈጥሩ የጥፋት አካሄዶች ናቸዉ፡፡ ለዚህም ነዉ ጓደኛዬ አነዚህን ሦስት ኃይሎች “የኢትዮጵያን አንድነት በዕገታ የያዙ ሦስት ተፃራሪ ኃይሎች” ብሎ የገለፃቸዉ፡፡

የኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ ሲመሠረት ባካተታቸዉና ለወደፊቱም በሚያካትታቸዉ ትክክለኛ የዲሞክራሲ ሥርዓትን የተረዱ ወይም የሚረዱ ህብረ-ብሔርና ብሔር-ተኮር የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ቡድኖች፣ ስብስቦችና ግለሰቦች የተቀናጀ ትግል አማካይነት የኢትዮጵያ አንድነት በፅኑ መሠረት ላይ የተገነባ እንዲሆን ይሠራል ተብሎ ይታመናል፡፡ በተቃዉሞ ፖለቲካችን ዉስጥ የተለመደዉ በጥቃቅን ልዩነቶችና ተራ አለመግባባቶች ምክንያት ተኮራርፎ ዛሬ የተመሠረተንና ተስፋ የተጣለበትን ስብስብ ነገ የማፍረስ አሣፋሪ ችግር ይህን ከአነሣሱ ከቀደምት ስህተቶች ትምህርት አግኝቶና የሕዝብን ጥያቄና ፍላጎት መሠረት አድርጎ የተነሣ የሚመስል አገራዊ ንቅናቄ አያጋጥመዉም የሚል ተስፋ በብዙዎች ዘንድ አሣድሯል፡፡ ስለሆነም ለዲሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ በሁሉም ልጆቿ የተባበረ ትግል በፅኑ መሠረት ላይ እንደ አዲስ መገንባት የማያወላዉል አቋም ያላቸዉ ወገኖች ሁሉ በንቅናቄዉ ጥላ ሥር ተሰባስበዉ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ከምንም በላይ የጠማቸዉን ነፃነት፣ እኩልነት፣ ፍትህ እና ያልተሸራረፈ የዲሞክራሲ መብት ለማጎናፀፍ ሌት ከቀን የሚሠሩበት ወቅት ነገ ሣይሆን ዛሬ ነዉ፡፡ ተከብሮ ለልጅ ልጆቻችን እንዲተላለፍ የምንፈልገዉን በሕዝቦች ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እዉነተኛ የኢትዮጵያ አንድነት ከሦስቱ ተፃራሪ ኃይሎች ዕገታ የማላቀቂያዉ መንገድም ይኸዉ ተባብሮ በጋራ የመታገል መንገድ ብቻ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

አቶ ዘውዴ ጉደታን በሚከተለው የኢሜይል አድራሻ ማግኘት ይቻላል ፤ [email protected]

 

Post your comment

Comments

Be the first to comment

Related Articles